ሊግ ኩባንያው በ8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በቀረቡ የሥነ ምግባር ጉዳዮችላይ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ በቀረቡ የሥነ ምግባር ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 8ኛ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች አምስት ጨዋታዎች በመሸናነፍ እና ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 23 ጎሎች በተቆጥረዋል።
በሳምንቱ 35 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች የማስጠንቀቂ ቢጫ ካርድ ሲሰጣቸው አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።
የሊግ ኩባንያው ውድድር አመራርና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ በተደረጉ ጨዋታዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የሥነ ምግባር ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የሲዳማ ቡናው ተጫዋች መክብብ ደገፉ ክለቡ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረገው ጨዋታ የተጋጣሚን ቡድን ግልፅ ግብ ዕድል በማበላሸት ከጨዋታ ሜዳ በቀይ ካርድ ተወግዷል፡፡
ተጫዋቹ ለፈፀመው ጥፋት በፌዴሬሽኑ ሥነ ምግባር መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ 3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል።
በክለቦች አርባምንጭ ከተማ እና ፋሲል ከነማ በሳምንቱ ጨዋታ የክለባቸው አምስት ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ 5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ መወሰኑን የሊግ ኩባንያው መረጃ ያመላክታል።