Fana: At a Speed of Life!

በኳታር የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ አድናቂዎችን ትኩረት የሳበው ኢትዮጵያዊ አርቲስት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2015 (ኤፍ  ቢ ሲ) ኢትዮጵያዊው አርቲስት ተሰማ አስራት በቀጥታ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ስዕል በመሳል በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ዋዜማ የእግር ኳስ አድናቂዎችን መሳብ ችሏል፡፡

ከቀናት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ከኳታር አል አናቢ የመጡ ደጋፊዎች የቡድናቸውን ድጋፍ ለማሳየት በዶሃ ሉሴይል ቦሊቫርድ ተሰበሰበው ነበር፡፡

በስፍራው ሲደርሱም ኢትዮጵያዊው አርቲስት ተሰማ አስራት የኳታር ብሄራዊ ቡድን አምበሉን ሀሰን አል ሃይዶስ ስዕል ወዲያውኑ ስሎ በማጠናቀቅ ደጋፊዎችን አስገርሟል፡፡

እኔ እግር ኳስን እወዳለሁ የሚለው ተሰማ  ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ናፋቂዎች መሆናቸውን እና ነገር ግን ኢትዮጵያ ከእግርኳሱ ይልቅ በአትሌቲክስ ውጤታማ መሆኗን አርቲስቱ ለፔኒሱላ የዜና ምንጭ ተናግሯል፡፡

ኢትዮጵያ በ2022 የዓለም ዋንጫ ማለፍ ባለመቻሏ ሁለተኛ ሀገሬ ናት የሚላትን የኳታር ሰንደቅ ዓላማ በዓለም ዋንጫው እንደሚያውለበልብ እና ድጋፉን እንደሚያሳይ ገልጿል፡፡

ኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሀገር መሆኗ በይፋ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ አርቲስቱ በስዕሎቹ እና በኪነ ጥበብ ስራዎቹ የዓለም ዋንጫውን ለማድመቅ ሲዘጋጅ መቆየቱንም አንስቷል፡፡

ለዓለም ዋንጫው ድምቀት ምን ማድረግ እንደምችል አሰብኩ፤ ከዛም እንደ አርቲስትነቴ በሥዕል ሥራ ችሎታዬን ተጠቅሜ ይህን ማድረግ እንደምችል አውቃለሁ፣ ወዲያውኑም የጥበብ መሣሪያዎቼን አዘጋጅቼ የዓለም ዋንጫው ወደሚካሄድበት ሉሴይል ቦሌቫርድ አመራሁ ብሏል አርቲስቱ።

ስራየን ሰዎች ሲያደንቁልኝ ደስታ ይሰማኛል የሚለው አርቲሰት ተሰማ ÷በስዕል ስራዎቹም የኢትዮጵያን ገፅታዎች ለማስተዋወቅ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡

አርቲስቱ  በተለያዩ የኪነጥበብ ትርኢቶች እና ውድድሮች በመሳተፍ ሽልማቶችን ያገኘ ሲሆን÷ በተለይም በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ጣሊያን፣ ሆላንድ፣ አየርላንድ፣ እንግሊዝ እና ኳታር የተካሄዱትን የኪነ ጥብበ ሽልማቶች ማሸነፉን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.