የአሜሪካ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ኮሮናቫይረስን ለመግታት ጥምረት ፈጥረዋል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ኮሮናቫይረስን ለመግታት በጥምረት ፈጥረው እየሰሩ መሆኑ ተሰምቷል።
በዚህም አማዞን ከማይክሮሶፍት ጋር በመተባበር የመመርመሪያ ቁሳቁሶችን በየሰዎች ቤት በማድረስ እና የሚሰበሰበውን ናሙና ለተመራማሪዎች መልሶ መውሰድ ስራውን ለመስራት ማሰባቸውም ነው የተነገረው፡፡
ቫይረሱ የተያዘ ሰው ከተገኘ ደግሞ ከጤና አጠባበቅ ሠራተኞች ጋር እንዲገናኝ ይደረጋል ተብሏል።
ስካን የተባለው የሕዝብ ጤና እና የምርምር ድርጅቶች ቡድን ወረርሽኙ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ እንዴት እንደሚሰራጭ ለማወቅ እየሞከረ ነው ተብሏል
በአሜሪካ ውስጥ በተከሰተው የኮሮና ቫረስ ወረርሽኝ በጣም ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ በዋንሽግተን ግዛት ውስጥ የሚገኘው ኪንግ ካውንቲ ነው ተብሏል።
በዚህም በጌትስ ፋውንዴሽን የሚደገፈው የሲያትል ኮሮናቫይረስ የምዘና አውታረ መረብ ወረርሽኙ እንዴት እንደሚሰራጭ በማጥናት ላይ ነው ተብሏል።
ጥናቱ ከአፍንጫ ናሙና መሰብሰብን ያካትታል ነው የተባለው።
የኩባንያዎቹ በጥምረት መስራት በአሜሪካ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ ምርመራን ለማሻሻል ሊረዳ እንደሚችልም ነው የተጠቆመው።
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል በሀገሪቱ ውስጥ 46 ሺህ 450 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ጠቁሞ፤ የሟቾች ቁጥር በእጥፍ 593 መድረሱን አስታውቋል።
ምንጭ፡-ቢ.ቢ.ሲ