አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ (2015) አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ በመካሄድ ላይ ነው።
ዋይት ሐውስ ፊት ለፊት እየተከናወነ በሚገኘው ሰልፍ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ኢዜአ ከሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሰላማዊ ሰልፈኞቹ አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተውን ዳግም ወረራ የሚያወግዙና “አሜሪካ የሽብር ቡድኑ እየፈጸመ ያለውን አፍራሽ ድርጊት በማውገዝ ተጠያቂ ማድረግ አለባት፣ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን መቆም ይኖርባታል” የሚሉ መፈክሮችን እያሰሙ ነው።
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያና በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ የምትከተለውን የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ዳግም ልታጤነው እንደሚገባ የሚያሳስቡ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው።
ሰልፋ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ያላቸውን አጋርነት የሚያሳዩበት ነው ተብሏል።
እንደዘገባው፥ ሰልፉን ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ አባላት፣ ከተለያዩ ተቋማትና ወዳጆች ጋር በመተባበር አዘጋጅቷል።