Fana: At a Speed of Life!

በሞጆ ደረቅ ወደብ ወደ ውጪ የሚላኩ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች የሚታሸጉበት ማዕከል ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሞጆ ደረቅ ወደብ ወደ ውጪ የሚላኩ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች የሚሰባሰቡበትና የሚታሸጉበት ማዕከል ሥራ ጀመረ።

የማዕከሉ ግንባታ በፍሬተርስ ኢንተርናሽናል የተከናወነ ሲሆን ፥ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ ዛሬ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።

የማዕከሉ መገንባት በየጊዜው እያደገ የመጣውን የወጪ ንግድ ምርት ጥራቱንና ደኅንነቱን በጠበቀ መልኩ ለማሰባሰብና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ከኢንዱስትሪ ዞኖች የተሰበሰቡ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች በቀላሉ ገዢዎች ባሉበት ሥፍራ እንዲደርሱ ለማድረግ ማዕከሉ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ነው የተናገሩት።

በዓለም ገበያ የሚፈለጉ ምርቶችን በፍጥነት ከማጓጓዝ ጎን ለጎን የላኪዎችን የሎጂስቲክስ ወጪ እስከ 40 በመቶ መቀነስ እንደሚያስችል መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የፍሬተርስ ኢንተርናሽናል ባለቤት አቶ ዳንኤል ዘሚካኤል በበኩላቸው፥ ማዕከሉ ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታቀርበውን የጨርቃ ጨርቅ ምርት የሚያሳልጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የማሰባሰብና የማቀናጀት ሥራ በሎጂስቲክስ ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የጠቆሙት ሃላፊው ፥ ማዕከሉ ምርቶችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳም ነው የጠቀሱት።

በተጨማሪም ሚኒስትሯ የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የግንባታ አፈጻጸም ጎብኝተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.