ኢሬቻ መልካ አቴቴ በቡራዩ በመከበር ላይ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢሬቻ መልካ አቴቴ በዓል በቡራዩ ከተማ በዛሬው ዕለት መከበር ጀምሯል።
የመልካ አቴቴ የኢሬቻ በዓል ከሆራ ፊንፊኔ እና ሆራ አርሰዲ ቀጥሎ በቡራዩ ከተማ የሚከበር በዓል ነው።
የመልካ አቴቴ ኢሬቻ በዓል የቡራዩ እና አካባቢው ነዋሪዎች፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የጋሞ አባቶች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
ኢሬቻ መልካ አቴቴ በተለየ መልኩ ሴቶች የሚያከብሩት በዓል ሲሆን ወንዶችም ይታደሙበታል።
ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ እየተከበረ በሚገኘው የመልካ አቴቴ በዓል ላይ ሀደ ሲንቄዎች፣ አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መታደማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የኢሬቻ በዓል የምስጋና፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የእርቅና የይቅርታ እና የኦሮሞ ህዝብ የሰላም እና አንድነት ምልክት መሆኑ ይታወቃል።