Fana: At a Speed of Life!

“ግድቤን በደጄ” የዝናብ ውሃን የማጠራቀም ፕሮጀክት ሥራ በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ ተጠቂ በሆኑ አካባቢዎች የሚተገበረው “ግድቤን በደጄ” የዝናብ ውሃን የማጠራቀም ፕሮጀክት ሥራ መጀመሩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋን ጨምሮ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቦረና ዞን ተግባራዊ መደረግ የጀመረውን ከጣሪያ ላይ ውሃ የማሰባሰብና ጥቅም ላይ የማዋል ፕሮጀክት ጎብኝተዋል፡፡

“ግድቤን በደጄ” በሚል መርህ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሙከራ ፕሮጀክት ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑ ተገልጿል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሐብታሙ ኢተፋ ÷”ግድቤን በደጄ” የዝናብ ውሃን የማጠራቀም ፕሮጀክት በቦረና ዞን በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና መንደሮች በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ከጣሪያ ላይ የዝናብ ውሃን በማሰባሰብ በዘመናዊ መንገድ ወደ ተገነባ ገንዳ በማጠራቀም ንጽህናው በተጠበቀ መልኩ በአነስተኛ ማሽን በማውጣት ሕብረተሰቡ እንዲጠቀም ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

በአሁኑ ጊዜ በቦረና ዞን ስምንት ትምህርት ቤቶችና ለአንድ አካባቢ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ በተለይ በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ አካባቢዎች ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ የውሃ እጥረት ባለባቸውና በተደጋጋሚ በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የፕሮጀክቱ ትግበራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.