የተለያዩ ሆስፒታሎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ጠያቂ እንዳይገባ ከለከሉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተለያዩ ሆስፒታሎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና የታካሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ።
ለአብነትም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የተገልጋዮችን ደህንነት ለመጠበቅ በአገልግሎታችን አሠጣጥ ላይ ለውጦች ለተወሰነ ጊዜ ማድረጉን በፌስቡክ ገፁ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ተኝተው ለሚታከሙ በሙሉ ከአንድ በላይ አስታማሚ ወደ ሕሙማን መኝታ ክፍልም ሆነ ወደ ቅጥር ግቢ መግባት እንደማይችል አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም በማታው ሲሰጥ የነበረው የግል ሕክምና ከትናንትናው እለት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን ያስታወቀው ሆስፒታሉ፤ የሕሙማን ጠያቂዎችን ላልተወሰነ ጊዜ ማስተናገድ ማቆሙንም ገልጿል።
የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታልም ለታካሚዎቻችን ደህንነት እና ጤና ሲባል ሆስፒታሉ ውስጥ በተለያዩ ህመሞች ተኝተው ህክምና እያገኙ ለሚገኙ ታካሚዎች ከአንድ
አስታማሚ በስተቀር ምንም ጠያቂ እንዳይገባ መከልከሉን አሳስቧል።
ይህንን በመገንዘብ በር አካባቢ በሚፈጠር አላስፈላጊ መጨናነቅ እና ግርግር ለኮሮና እና መሰል ተላላፊ በሽታዎች ስለሚያጋልጡ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ሲልም አሳስቧል።
ሌሎች ሆስፒታሎችም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና የታካሚዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ወደ ቅጥር ግቢያቸው የሚገቡ ሰዎችን የሰውነት ሙቀል ልየታ ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።