Fana: At a Speed of Life!

በአፋር ክልል የፖሊዮ መከላከያ ክትባት የመስጠት ዘመቻ ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 23 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ውስጥ በነበሩ 11 ወረዳዎች የፖሊዮ መከላከያ ክትባት የመስጠት ዘመቻ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
 
የፖሊዮ ክትባት መርሐ ግብሩ ለአራት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ÷ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ100 ሺህ በላይ ሕጻናት እንደሚከተቡ ተገልጿል።
 
የአፋር ክልል ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈረጅ ረቢሳ ክትባቱን በማሂ-ረሱ ዞን ያንጉዲ ወረዳ አስጀምረዋል።
 
ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ ባለፈው ዓመት በ28 ወረዳዎች ከ187ሺህ በላይ ህጻናት የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዙር የፓሊዮ መከላከያ ክትባት መውሰዳቸውን አስታውሰዋል።
 
በወቅቱ በህወሓት የሽብር ቡድን ወረራ ተይዘው በነበሩ 6 ወረዳዎች እና በሌሎች የጸጥታ ችግሮች ውስጥ የነበሩ ሌሎች ወረዳዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 11 ወረዳዎች ላይ ክትባቱ ሳይሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል።
 
አሁን በአካባቢዎቹ የጸጥታ ሁኔታው አንጻራዊ መሻሻል በማሳየቱ የመጀመሪያው ዙር የፓሊዮ መከላከያ ክትባት ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 4 ቀናት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።
 
ክትባቱ በየአካባቢዎቹ በሚገኙ ጤና ተቋማትና የተመረጡ ህዝብ የሚበዛባቸው ማዕከሎችን ጨምሮ ቤት ለቤት እንደሚሰጥ ነው የጠቆሙት።
 
ዳይሬክተሩ አመራሮ፣ የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ መሪዎች ለክትባቱ ውጤታማነት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.