የአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ የአስክሬን ሽኝት መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ የአስክሬን ሽኝት መርሐ ግብር ከመኖሪያ ቤቱ ጀምሮ እየተካሄደ ነው፡፡
ከአርቲስቱ መኖሪያ ቤት ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የአስክሬን ሽኝት መርሐ ግብር÷ በመቀጠልም በወዳጅነት ፓርክ በመንግሥት ባለስልጣናት፣ በሙያ አጋሮቹ፣ በአድናቂዎቹ እና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት የአስክሬን ስንብት ይካሄዳል።
የተወዳጁ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርአት በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።
ተወዳጁ የጥበብ ሰው ማዲንጎ አፈወርቅ ስለ ፍቅር፣ ትዝታ፣ ባህል፣ ሀገር፣ ታሪክና ሌሎች ጉዳዮችን የሚዳስሱ መልዕክቶችን በተስረቅራቂ ድምጹ በማዜም በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ስራ ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል።
ማዲንጎ አፈወርቅ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወቅት እያመመው ግንባር ድረስ በመሄድና ማሰልጠኛም ምልምሎችን በማነቃቃት የራሱ የሆነ ታሪክ የሰራ አርቲስት መሆኑም ይታወቃል።
በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር አዘዞ ተወልዶ በደብረታቦር ያደገው አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ መስከረም 17 ቀን 2015 ዓ.ም ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።