ቀጣይነት ያለው የጤና ስርዓት እንዲኖር የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ጠንካራና ቀጣይነት ያለው የጤና ስርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ድርሻ ስላለው ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ፡፡
በአዳማ ከተማ የተካሄደው የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ዓመታዊ የጤና ጉባዔ ተጠናቋል።
ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ÷ሀገር አቀፍ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ፍኖተ ካርታ ወጥቶ እየተተገበረ መሆኑን አንስተው ፥ በአንዳንድ አካባቢዎችም የፕሮግራሙ አተገባበር ላይ መቀዛቀዝ እየታየ በመሆኑ እንዲጠናከርም ነው ያሳሰቡት።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተለይም ተላላፊ በሆኑ እንደቲቢ፣ ኤች አይቪና የኮቪድ 19 ወርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሰራው ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ የጸጥታ ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን ጨምሮ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የተጠናከረ የቅኝትና የመከላከል ስራ መሰራት አለበትም ነው ያሉት፡፡
የጤና ስራ ቁርጠኝነትንና የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን ስለሚፈልግ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዶ/ር ደረጀ መጠየቃቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነመራ ቡሊ በበኩላቸዉ÷ በክልሉ የተያዘውን ልማትና ብልጽግና ማሳካት የሚቻለው ጤናማና አምራች የሆነ ህብረተሰብ መፍጠር ሲቻል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ በመድረኩ ላይ አዲስ ሎጎ ይፋ ያደረገ ሲሆን÷በ2014 የተሻለ የስራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ዞኖችና ተቋማትም እውቅናና ሽልማት ተበርክቷል፡፡