በክልሎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ እስካሁን በክልሎች ባይከሰትም ክልሎች ቫይረሱን ለመከላከል የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየሰሩ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።
የዓለም የጤና ስጋት እና ወረርሽኝ የሆነው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ በ6 ሰዎች ላይ ተገኝቷል።
የቫይረሱን ወደ ኢትዮጵያ መግባት ተከትሎ እንደ ሀገር የስርጭት መጠኑን ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎም ክልሎች የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ አፋር እና የሀረሪ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ክልል ጉራጌ እና ስልጤ ዞኖች ቫይረሱን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑን ለጣቢያችን ገልጸዋል።
በዚህም ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ የንግድ ተቋማት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንና ህብረተሰቡ ጥንቃቄው ላይ ጥሩ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የአፋር ክልል በአየር እና በየብስ የሚገቡ መንገደኞችን ሙቀት የመለካት ስራ እያከናወነ መሆኑንና የለይቶ ማከሚያ ማዕከል ማዘጋጀቱን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
የቅድመ ጥንቃቄ ስራውን የሚከታተል እና ስራውን የሚገመግም ግብረ ሀይል እስከ ወረዳ ድረስ መቋቋሙንም ነው የተናገሩት።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በጅቡቲ ድንበር ጋላፊ ኬላ ላይ የተቋቋመው የሙቀት መለኪያ ጣቢያ እስከ ዛሬ ድረስ 45 ሺህ ሰዎችን ሙቀት የመለየት ስራ ማከናወኑን አስታውሰዋል።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፥ ቫይረሱ በክልሉ እንዳይከሰትና ከተከሰተም የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስራዎችን እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ከግብአት ጋር ተያይዞ በተለይም ለአቅመ ደካሞች እንዲቀርብላቸው ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ የውሀ እጥረት እንዳይከሰትም የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አስረድተዋል።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆኑን የከተማው ምክትል ከንቲባ ከድር ጃዋር ለጣቢያችን ገልፀዋል።
አቶ ከድር በከተማ አስተዳደሩ በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎች ተገኝተው እንደነበር አስታውሰው፥ በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ እንደሆኑ መረጋገጡን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የለይቶ ማከሚያ ጤና ጣቢያ መዘጋጀቱንና በቂ ስላልሆነ ተጨማሪ ሆስፒታል ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አውስተዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጉራጌ እና ስልጤ ዞኖች የኮሮና ቫይረስን መከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።
የየዞኖቹ ጤና ቢሮዎች ኮሮና ቫይረስን በተመለከተ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ እንዲሁም ግብአቶች እንዲቀርቡ የሚያመቻች ግብረ ሃይል አቋቁመው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
በዙፋን ካሳሁን እና አወል አበራ
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision