Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ- የሱዳን የህዝብ ለህዝብ ማጠናከሪያ መድረክ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦችን የህዝብ ለህዝብ የሚያጠናክር የውይይት መድረክ ተጀመረ።

የመጭው ዘመን ትውልድ የአፍሪካ አንድነትን እንዲያጠናክር ያለመ እና በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በተለያዩ ኤምባሲዎች የሚካሄደው የወንድማማችነት ሁነት በአዲስ አበባ ሱዳን ኤምባሲ መካሄድ ጀምሯል።

ዛሬ በተጀመረው ዝግጅት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል እና የዝግጅቱ ዐብይ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል ባደረጉት ንግግር ሁነቱ በአፍሪካ ሃገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኘነት ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይት መረሃ ግብሩ ረጅም ዘመን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኘነት በየወቅቱ በሚፈጠሩ ችግሮች ሳይወሰን የጋራ እሴቶችን በማጉላት በዘላቂነት እንዲጠናከር ለማስቻል አስተዋፅኦ ይኖረዋል ሲሉም ነው ያመለከቱት።

በኢትዮጵያ የሱዳን ኤምባሲ አምባሳደር ጀማል አሸር አህመድ ደግሞ የሃገራቱን ነባር ግንኙነት ይበልጥ የህዝቦቹን ወዳጅነት እና ትስስር ለማጠንከር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመረሃግብሩ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሱዳን ኮሚኒቲ አባላት፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ዲፕሎማቶ የቀድሞ አምባሳደሮች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች መገኘታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.