Fana: At a Speed of Life!

ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በመዲናዋ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በመዲናዋ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በልዩ ሁኔታ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሚቴው የውሃ እና ፍሳሽ ስራውን የሚቆጣጠር፣ የሚከታተል፣ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ደህንነት ላይ የግንዛቤ እና የጥንቃቄ ስራ የሚያከናውን ነው ተብሏል።

የባለስልጣኑ ዋና ስራ ስኪያጅ ኢንጅነር ዘሪሁን አባተ ባለስልጣኑ በኳራንቲን የተለዩ የጤና ተቋማት እና በመዲናዋ የሚገኙ ትላልቅ ሆስፒታሎች ጋር በየቀኑ ግንኙነት በማድረግ በውሃ አቅርቦት እና ፍሳሽ ማንሳት ላይ ልዩ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረዋል።

ውሃ በፈረቃ በሚታደልባቸው አካባቢዎች በቅርበት በመስራት ደንበኞች በፈረቃቸው እያገኙ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በፈረቃቸው ካላገኙም በቦቴ እስከ ምሽት 6 ሰዓት ለዚሁ አላማ በተዘጋጁ 28 የውሃ ቦቴ ተሽከርካሪዎች ለማዳረስ ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት።

እንዲሁም ህዝብ በብዛት የሚንቀሳቀስባቸው ቃሊቲ፣ አስኮ፣ መርካቶ፣ ዘነበ ወርቅ እና ላምበረት በሚገኙ አውቶብስ ተራ ከነገ ጀምሮ የእጅ መታጠብ መርሀ ግብር ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በባለስልጣኑ ስር የነበሩ እና አሁን በሌላ ተቋም በሚተዳደሩ ህዝብ የሚበዛቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተንቀሳቃሽ መጸዳጃ ቤቶች፥ ህዝቡ እጁን እንዲታጠብ ለመጋቢት ወር ውሃ በነጻ እንደሚያቀርብ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.