የልጆች የመጀመሪያዎቹ የትምህርት ቀናት ውሎ እና ከወላጆች የሚጠበቁ ተግባራት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማና በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች የ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
ታዲያ በዚህ ወቅት በተለይም ለመጀመሪያ ጊዜ የትምህርት ቤት ደጃፍ የሚረግጡ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ሲገቡ የተለያዩ ባህሪዎችን ያሳያሉ፡፡
በዚህ ዙሪያ በብሩህ ተስፋ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት ተጠሪ መምህርት ጥበበ ሰለሞን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
እንደ መምህርት ጥበበ ገለፃ በመጀመሪያዎቹ የትምህርት ቀናት ልጆች ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ስለሚመለከቱ ያለቅሳሉ፣ ወላጆቻቸውን አለቅም ብለው ያስቸግራሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ቶሎ ወደ መጫወቻ ስፍራ ይሮጣሉ፡፡
ለዚህም ወላጆች ልጆችን በስነልቦና ማዘጋጀት እና ቢቻል የትምህርት ቤቱን ነባራዊ ሁኔታ ማሳየት፣ በትምህርት ቤት ውስጥ እውቀት እንደሚቀስሙ እና ብዙ ጓደኞች እንደሚያፈሩ፣ እንደሚጫወቱ ቢነግሯቸው መልካም መሆኑን ይናገራሉ።
ይህን ማድረጉ ደግሞ ልጆች ጉጉት እንዲያድርባቸው ያደርጋል ነው ያሉት መመህርቷ፡፡
በሌላ በኩልም ብዙ ምሳ እቃ አስይዞ መላክ ትክክል እንዳልሆነ እና ልጆች በአቅማቸው የተመጣጠነ ምግብ (እንደ ወላጅ አቅም) እንዲመገቡ ማድረግ እመንደሚገባ መክረዋል፡፡
እንዲሁም የአመጋገብ ስርዓትን፣ የሽንት ቤት አጠቃቀምን፣ ልብስ አለባበስን እንዲሁም ደረጃ አወጣጥን ልጆች ተለማምደው ወደ ትምህርት ቤት ቢመጡ ስራዎችን ያቀላሉ ባይ ናቸው።
መምህራንም ተማሪዎችን በእድሜያቸው እና ስርዓተ ትምህርቱ ባስቀመጠው መሰረት በፍቅር፣ በጨዋታ ዕውቀትን ማስቀሰም እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
በፌቨን ቢሻው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!