የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ለመከላከል የዳያስፖራው ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ለሚደረገው እንቅስቃሴ ያልተገቡ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ለመከላከል የዳያስፖራው ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።
የዳያስፖራ ፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ንቅናቄ ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ የኢፌዴሪ አምባሳደሮች፣ የሚሲዮን መሪዎች፣ የዳያስፖራ አደረጃጀት ሃላፊዎችና አባላት በበይነ መረብ ተወያይተዋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ÷ መንግስት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የጀመራቸውን ስራዎች በማንኛውም ቦታና ሁኔታ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስከበር ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የተሳሳተ ትርጉም በመስጠት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚፈጠሩ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመከላከል ዳያስፖራው የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን እውነት ለማስረዳትና የሽብር ቡድኑን ህወሓት ባህሪና የፈጸማቸውን ጥፋቶች ለማጋለጥ ዳያስፖራው የሚጠበቅበትን ሚና ማበርከት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
ዳያስፖራው የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ለመደገፍና የመረጃ ስርጭት ስርዓቱን ለማሻሻል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ በበኩላቸው÷መድረኩ ያልተገቡ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ለመመከትና የኢትዮጵያን እውነት ለማስረዳት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ያሉበት ሁኔታ ላይ በመወያየት ስራዎቹን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ሳምንታት ዳያስፖራው ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎችም አበረታች ውጤቶች መመዝገብ መጀመራቸውን አንስተው÷ዳያስፖራው ካካበተው የማድረግ አቅምና የጫናው ግዝፈት እየጨመረ የሚሄድ ከመሆኑ አንጻር ስራው ይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል ።
በዚህ ረገድ መንግስት ዳያስፖራው የሚያደርጋቸውን ጥረቶች በልዩ ልዩ አግባቦች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ከዲጂታል ምህዳሩ በተጨማሪ በመደበኛ ሚዲያዎች ላይ ያለውን ተሳትፎ ሊያሳድግ እና ዘመቻዎቹ የተናበቡና ሀገራዊ ጥቅሞችን ያስቀደሙ ሊሆኑ እንደሚገቡ መገለጹንም ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡