በ22 መድኃኒት ቤቶች እና መደብሮች ላይ እርምጃ ተወሠደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ230 መድኃኒት ቤቶችና መድኃኒት መደብሮች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ቁጥጥር በ22 ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሠደ።
የኮሮና ቫይረስ በሀገራችን መከሰቱን ተከትሎ በሸቀጦች ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን የሚቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቁሟል።
ግብረ ሃይሉ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት መጋቢት 7 እና 8 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከፊት ጭምብል፣ የእጅ ንጽህና መጠበቂያና ጓንት ጋር በተያያዘ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ አካላት ላይ እርምጃ ወስዷል።
በዚህም በ230 መድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ላይ በተደረገ ድንገተኛ የቁጥጥር ስራ 22 ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል።
በተጋነነ ዋጋ ሲሸጡ በተገኙ እና በድርጅታቸው ውስጥ አቅርቦቱ እያለ የለንም ያሉ ሰባት ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን 15ቱ ደግሞ እንዲታሸጉ ተደርገዋል።
በሌላ በኩል አንድ ድርጅት ከክፍለ ከተማ ከወሰደው የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ውጭ ያልተፈቀደለትን እና ደረጃውን ያልጠበቀ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ እያመረተ በመገኘቱ ማምረቱን እንዲያቆም በማድረግ ምርቱ ከገበያ ተሰብስቧል።
በተመሳሳይ አንድ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያ አስመጭና አከፋፋይ ጓንት መግዛት ለሚፈልጉ ደንበኞች ሌሎች መድኃኒቶችን ያለፍላጎታቸው ጨምረው እንዲገዙ በማድረጉ እርምጃ መወሰዱን ከኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision