Fana: At a Speed of Life!

ሃሰተኛ ገንዘብ እና ሌሎች ሰነዶችን እያተመ ሲያሰራጭ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

 

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃሰተኛ ገንዘብ እና ሌሎች ሰነዶችን እያተመ ሲያሰራጭ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

 

ፖሊስ ከዚህ ቀደም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሶስት ግለሰቦች 396 ሀሰተኛ ባለ 200 መቶ የብር ኖቶችን ይዘው በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ አስታውቋል።

 

የሃሰተኛ ገንዘቡን ምንጭ ለማወቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በመቀናጀት ባደረጉት ክትትል ሃሰተኛ ገንዘብ እና ሌሎች ሰነዶችን እያተመ ሲያሰራጭ የነበረው ታምራት ሃይሌ የተባለ ግለሰብ ሃሰተኛ ገንዘብ እና ሰነዶቹን በሚያትምበት ቤት ውስጥ በቁጥጥር ስር ውሏል።

 

ግለሰቡ በክፍለ ከተማው ወረዳ 14 ልዩ ቦታው ግራር መስቀለኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ መሆኑንም ነው ፖሊስ የገለጸው።

 

ግለሰቡ በመኖሪያ ቤቱ ሃሰተኛ የአሜሪካ ዶላር፣ የተበላሹ ሃሰተኛ ባለ ሁለት መቶ የብር ኖቶች፣ የልደት የምስክር ወረቀቶች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ማስረጃዎች እና ሌሎች ልዩ ልዩ ሰነዶች ተገኝተዋል፡፡

 

በተጨማሪም የወረዳ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ የግል እና የመንግስት ተቋማት ማህተሞችን ለመቅረፅ እና ሀሰተኛ ገንዘቦችን ጨምሮ ልዩ ልዩ ህገ ወጥ ሰነዶችን ለማተም የሚጠቀምባቸው ቁሳቁሶች እንደተያዙም የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.