በ461 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የዓይን ህክምና ማዕከልተመረቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል በ461 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቁ እና ዘመናዊ የአይን ህክምና ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡
ማዕከሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው በዛሬው ዕለት የተመረቀው፡፡
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ÷“የከተማ አስተዳደሩ በሀገራችን ሰፊ ችግሮች የነበሩበትን የአይን ህክምና አገልግሎት ለማሻሻል እና ለማሳደግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል በ461 ሚሊየን ብር ወጪ በሀገራችን ደረጃ ትልቁና ዘመናዊ የአይን ህክምና ማእከል ገንብቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ብቁ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
ማዕከሉ የከተማዋ ብቻ ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ ያለውን የዓይን ህክምና አገልግሎት በጥራትም በተደራሽነትም ይሁን በቅልጥፍና በእጅጉ የሚያሳድገው መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የአይን ህክምና ማዕከሉ ሁሉንም አይነት የዓይን ህክምና አገልግሎቶች በአንድ ህንፃ ውስጥ የሚሰጥ መሆኑ ነው የተገለጸው፡
በሌላ በኩል ማዕከሉ በ8 የተመላላሽ ክፍሎች ውስጥ ህክምና ሲሰጥ የነበረውን ወደ 33 ክፍሎች ከፍ በማድረግ አቅሙን በ 4 እጥፍ ያሳደገ ሲሆን ÷የመኝታ አልጋዎችም ከ40 ወደ 120 አልጋዎች ከፍ ማለታቸው ተጠቁሟል፡፡
በአይን ህክምና ላይ ሲታይ የነበረውን የተራዘመ ቀጠሮ የሚያስቀርና እንግልትን የሚቀንስ እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሪፈር የሚመጡትን በተደራጀ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል፡፡