Fana: At a Speed of Life!

በአገራችን ያለውን የሰላም እጦት ለመቅረፍና በምግብ ራስ የመቻል ስራን እውን ለማድረግ በቅንጅት መስራት ይገባል – አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገራችን ያለውን የሰላም እጦት ለመቅረፍና የተጀመረውን በምግብ ራስ የመቻል ስራ ፍሬ እንዲያፈራ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

አፈ ጉባኤው የ2015 አዲስ ዓመትን አስመልክተው ለመላው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም፥ አዲሱ ዓመት የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያውያን በሁለንተናዊ መልኩ ታትረው የሚሠሩበትና ለሀገራችን ሠላም፣ ብልጽግናና አንድነት መሠረት የሚጥሉበት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብዘሃ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶችና ማንነቶች ያሏት ህብራዊነቷ መገለጫዋና ማጌጫዋ፣ አንድነቷ ደግሞ ብርታቷና ጽናቷ አድርጋ ለዘመናት የኖረች ሀገር መሆኗንም አውስተዋል አፈ ጉባኤው፡፡

በኢትዮጵያ ለዘመናት ተዋደውና ተዋህደው፣ ተጋምደውና ተዋልደው በኖሩ ህዝቦች መካከል ባለፈው ስርዓት ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ከአብሮነት ይልቅ መለያየት ሲሰበክ በመኖሩ ሀገራችን ከሰላም ይልቅ የጦርነትና የግጭት አውድማ ሆና ቆይታለች ሲሉም አንስተዋል ፡፡

ከዚህ ባለፈም ህዝቦቿ በበቀሉባት ሀገር፣ እንግዳ በኖሩበት ቀየ ባዳ ሆነው ለመኖር ተገደዋል፤ ውሎ መግባት ብርቅ፣ ኖሮ መሞት ድንቅ ለመሆን በቅቶ ነበር ነው ያሉት።

በአዲሱ ዓመት በሚካሄደው ሀገራዊ ምክክርም፥ ባለድርሻ አካላት በስክነት፣ በብስለት፣ በአርቆ አስተዋይነትና ሰጥቶ በመቀበል መርህ አገራችንን ከገባችበት የሰላም እጦትና የድህነት ቅርቃር አውጥተን ወደቀደመው የከፍታ ዘመኗ እንድትመለስ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

“ኢትዮጵያውያን ብዘሃነታችሁን ለጋራ መዋቢያና መድመቂያ እንጂ ለልዩነት ድንበር ማበጂያ ሳታውሉት እንደቀደሙት አባቶቻችን በመቻቻልና በመረዳዳት መንፈስ በአንድነት ጸንቶ በመቆም የኩሩነትና የአይደፈሬነት ታሪካችንን ማስጠበቅ ይኖርብናልም” ነው ያሉት።

በተለይም በአሁኑ ጊዜ ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ከውስጥ ባንዳዎች የተቃጣብንን አገራችንን የማፈራረስ ጦርነት እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን ልናከሽፈውና ልንመክተው ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡፡

“ከዚህም ጎን ለጎን የተጀመረውን በምግብ ራስን የመቻል፣ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች፣ የአረንጓደኤ አሻራ ስራችን አጠናክረን በመስራት በሁለንተናዊ መልኩ ተገዳዳሪና ተፈሪ ሀገር መፍጠር ይጠበቅብናል” ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.