አዲሱ ዓመት ለሀገራችን ከፍታ የምንተጋበት ዘመን ይሆናል – አቶ ርስቱ ይርዳ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ የ2015 ዓ.ም አዲስ አመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
አቶ ርስቱ ፥ በመልዕክታቸው “አዲሱ ዓመት ለሀገራችን ከፍታ የምንተጋበት፣ የተቸገሩ ወገኖቻችንን የምንረዳበት የመተሳሰብ እና የአንድነት ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ” ብለዋል።
አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ የከፍታ ዘመን ለህዝቦቿ አንድነት እና ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበት ዘመን እንዲሆንም ነው የተመኙት።
“2014 ዓ.ም በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን እቅዳችንን በስኬታማነት የፈፀምንበትና በርካታ ተግባራትን በውጤታማነት ያከናወንበት አመት ነበር” ብለዋል።
ሀገር የማፍረስ ተልዕኮን ያነገበው አሸባሪው ህወሓት በሀገራችን ላይ የሰነዘረውን ወረራ የክልላችን ህዝቦች ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበር በመመከት ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደቻሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።
ባገባደድነው 2014 በጀት አመት የመንግስት ምስረታውን ውጤታማ ማድረግ ከመቻሉም ባሻገር በልማት ስራዎች በግብርና በመሰረተ ልማት እና በኢንቨስትመንት ዘርፎች መላው የክልሉን ህዝብ በማሳተፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችለናል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች በክልል የመደራጀት የዘመናት ጥያቄ የተመለሰበት ዓመት እንደነበረም አስታውሰዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በአደረጃጀት፣ በሐይማኖት፣ በወሰንና በሌሎች ምክንያቶች የተፈጠሩትን የፀጥታ ችግሮች በጠንካራ ሕግ የማስከበር ስራ እና በህብረተሰቡ የቆየ ባህላዊ የእርቅ ስነ -ስርዓት መፍታት እንደተቻለም ነው ያመለከቱት።
እንደ ሀገር ባገባደድነዉ አመት በርካታ ተግዳሮቶች ቢገጥሙም በጋራ እና በአንድነት በመቆም የሽብር ቡድኑን ሴራዎችን አክሽፈን አሁን ያለንበት ጊዜ ላይ ደርሰናልም ነው ያሉት።
2015 የህወሃት የሽብር ቡድን ለሦስተኛ ጊዜ የሰነዘረብንን ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ የምንመክትበት እና ኢትዮጵያን የመበተን ህልሙን ቅዠት የሚናደርግበት ይሆናል ብለዋል።
“በልማት ግንባሩም ጠንክረን የምንሰራበት አጠቃላይ የጠላትን አጀንዳ በመዝጋት ተኩረታችንና ርብርባችንን ልማት ብልፅግና ላይ የምናደርግ ይሆናል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።