የኮሮና ቫይረስን የተመለከተ ዜና ሲከታትል የማስታወስ ችሎታው የተመለሰለት ወጣት
አዲስ አበባ፣መጋቢት 8፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በፈረንጆቹ 1990 በደረሰበት የአዕምሮ ጉዳት የማስታወስ ችሎታውን ያጣው ወጣት ቻይናዊ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን የተመለከተ ዜና ሲከታተል የማስታወስ ችሎታው መመለሱ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡
ዙ ጂያሚንግ የተባለው ይህ ግለሰብ ከሠላሳ ዓመታት በፊት ከደቡብ-ምዕራብ ቻይና ከሚገኘው መኖሪያው የግንባታ ስራ ለመስራት ወደ ማዕከላዊው ሃቤይ መሄዱ ተነግሯል፡፡
ሆኖም ወጣቱ በዚያው ዓመት በስራ ቦታ በደረሰበት ከባድ አደጋ የአእምሮ ጉዳት ደርሶበት ለረዥም ጊዜ በመርሳት ህመም ሲሰቃይ ቆይቷል ነው የተባለው፡፡
በሽታው ባስከተለው ችግር ያለፈው ህይወቱን ለማስታወስ ቢጥርም ፣ ስለ ቤቱም ሆነ ስለ ቤተሰቡ ማንኛውንም ነገር ማስታወስ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡
ማንነቱን የሚገልፅ መታወቂያ የጣለው ዙ ጂያሚንግ ቅን የሆኑ ባለትዳሮች አብሯዋቸው እንዲኖር ከማድረጋቸው በፊት ኑሮውን በጎዳና ላይ ማድረጉ ተሰምቷል ፡፡
በርካታ ዓመታት ምንም ነገር ሳያስታወስ ህይወቱን ሲገፋ የነበረው ወጣቱ አለምን በከፍተኛ ሁኔታ እያስጨነቀ የሚገኘው ኮሮና ቫይረስ ለእሱ መልካም እድልን አምጥቶለታል።
ይህም ባለፈው ወር በትውልድ ከተማው ስለተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚገልጽ ዜና ሲመለከት÷ ዚ ጂያሚንግ በድንገት የቀድሞ ቤቱን ማስታወሱ ተነግሯል፡፡
ወዲያውም እርዳታ ለማግኘት ወደ ፖሊስ ማምራቱም ነው የተገለፀው፡፡
በዚህም ዚ ጂያሚንግ ከእናቱ እና ከአራት እህቶቹ ጋር እንደገና መገናኘት መቻሉ የተገለጸ ሲሆን አባቱ ከ18 ዓመታት በፊት መሞቱን ተረድቷል።
ዙ በትውልድ ቦታው ለብዙ ዓመታት በመጥፋቱ የመኖሪያ ፈቃዱ ተሰርዞ ነበረ።
የ83 ዓመት አዛውንት የሆኑት የዙ እናትም በቪዲዮ የስልክ ጥሪ መቼም አገኝሃለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፤ መኖርህን በማወቄ በጣም ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡
ዙ በመጨረሻም ወደ ትውልድ አካባቢው ለመመለስ የመኖሪያ ፈቃዱ እስኪታደስ ድረስ እየጠበቀ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ምንጭ፡-ኦዲቲ ሴንትራል