በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቋመ
አዲስ አበባ መጋቢት 8፣ 201 2(ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ የሚመራ ግብረ ሃይል መቋቋሙን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
የአማራ ክልል የሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ በክልሉ ያለውን ሰላም በዘላቂነት ማስቀጥል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር ተወያይቷል።
በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች እና የተለያዩ ሃይማኖት ተቋማት አባቶች ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅትም በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መልካሙ አብጤ ተናግረዋል።
በዚህ መሰረትም በክልሉ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ የሚመራ ግብረ ሃይል መቋቋሙን ነው የገለጹት።
በጎንደር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ላሊበላና ባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዲሁም በመተማ ሱዳን ድንበር የልየታ እና የቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
የተቋቋመው ግበረ ሃይል የትራንስፖርት እጥረት እንዳይኖር እና የመድሃኒት ዋጋ እንዳይጨምር ከከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያዎች በባህር ዳር እና ደሴ የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማዕከሎች መኖራቸውን የገለፁት ሃላፊው፥ ኬሚካሎችን የማስመጣት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በመረጋጋት የበሽታውን የመከላከያ መንገዶች በትክክል መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል።
በናትናኤል ጥጋቡ