ህወሓት በተለያዩ አካባቢዎች ማህበራዊ ሽብር ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አፈትልኮ የወጣው የራሱ ሰነድ አጋለጠ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ማህበራዊ ሽብር ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አፈትልኮ የወጣው የራሱ ሰነድ አጋልጧል፡፡
አሸባሪው ህወሓት “የማጠቃለያ ምዕራፍ አካሄድና ስትራቴጂ” በሚል በድብቅ አዘጋጅቶ ለበታች አመራሩ የበተነው ሰነድ እንዳመላከተው÷ በተለያዩ አካባቢዎች የተቀናበሩ የሽብር ድርጊቶችን ለመፈጸም እና ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር ከውጪ እና ከሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ጋር እየሰራ ነው፡፡
ለዚህም መንግስት በኢኮኖሚ ዘርፍ የጀመረውን የእርሻ ልማት፣ ስንዴና ሌሎች የልማት ስራዎችን ለማደናቀፍ ልዩነቶችን ተጠቅሞ በየአካባቢው ግጭት እና ሽብር መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ነው ሰነዱ የጠቆመው፡፡
ይህ አላማ ግቡን ይመታ ዘንድም በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ለመቀስቀስ የሚያስችሉ ሃይሎች ማሰማራት፣ ማገዝ እና ማስታጠቅ ላይ እንደሚሰራ አመላክቷል፡፡
በአማራ ክልል የቅማንት የወሰንና ማንነት ጉዳዮችን በሚመለከት ከፍተኛ ሕዝባዊ ጥያቄ እንዲነሳና አካባቢውን ወደማያባራ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግር ውስጥ እንዲገባ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚያከናውን በሰነዱ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪ ም ወደ አማራ ክልል በተፈናቃይና በተጓዥ ስም የሚገባ ሃይል በማዘጋጀት የሽብር ስራ በጥንቃቄ እንዲሰራ ከማድረግ ባለፈ ወደ አዲስ አበባ ዙሪያ እንዲጠጋ እንደሚያደርግም ነው ያመላከተው ሰነዱ።
በህወሓትየሥልጣን ዘመን ያልተመሱ በርካታ የአደረጃጀት ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት በሰላማዊ መንግድ እልባት እያገኙ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ህወሓት በራሱ የስልጣን ዘመን መመለስ ያልቻለውን በተለይም በደቡብ ክልል የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ወደ ግጭት በመቀየር ለራሱ ፍጆታ የመጠቀም ፍላጎት እንዳለው በዚሁ ሰነድ ተጋልጧል፡፡
ሰነዱ “በደቡብ ክልል እየታየ ያለውን የክልልነት ጥያቄ በደንብ እንዲጠናከር በማድረግ እንዲሁም ተመሳሳይ የክልልነት ጥያቄዎች በተጠናና በተናበበ መልኩ በሌሎች አካባቢዎች እንዲነሱ ማድረግ” ሲል የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ወደ ግጭት የመቀየር ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡
ህዝቡ በመንግስት ላይ እንዲነሳ ለማድረግም የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮችን በተቀናጀ መንገድ መፈጸም አስፈላጊ መሆኑን ነው ሰነዱ ያብራራው፡፡
ለዚህም የተመረጡ አምራች ድርጅቶችንና መጋዝናቸውን ማቃጠል፣ የዕለት አስቤዛ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖረው ማድረግ፣ ከውጪ የሚገቡ ሸቀጦች እና ነዳጅ እንዲስተጓጎል ዋና ዋና የማስገቢያ ኮሪደሮች በመቆጣጠር ሌሎች እርምጃዎችን እንደሚወስድ መግለጹ የቡድኑን ትክክለኛ የሽብርተኝነት ባህሪ የሚያሳይ ነው፡፡