Fana: At a Speed of Life!

በሐይቅ ውስጥ የተገኘችው ጥንታዊ የኢራቅ ከተማ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ድርቅ እያጠቃት በምትገኘው ኢራቅ ውስጥ ግዙፍ ቤተ መንግስት ያለው ጥንታዊ ከተማ ከሐይቅ ውስጥ ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።

ለዓመታት የዘለቀው ድርቅ በቅርቡ በኢራቅ ውስጥ በውሃ ሥር የሚገኙ በርካታ ከተሞች እንዲታዩ አድርጓል።

ጥንታዊቷ ከተማ በሰሜን ኢራቅ ኩርዲስታን ክልል በከሙኔ አቅራቢያ በሚገኘው የሞሱል ግድብ መገኘቷን የጀርመን እና የኩርዲሽ አርኪዮሎጂስቶች ቡድን ይፋ አድርጓል።

የ3 ሺህ 400 ዓመታት ዕድሜ እንዳላት የተነገረላት አነስተኛ ከተማ ኢራቅን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ1550 እስከ 1350 ዓመተ ዓለም ድረስ ባስተዳደረው ሚታኒ ስርወ – መንግስት ወቅት አስፈላጊ የነበረችው የዛኪኩ ከተማ ሳትሆን እንደማትቀርም ነው የተገለጸው።

ከተማዋ ፈዘዝ ያለ ቡኒ እና አቧራማ የከተማው ፍርስራሽ ቤተ መንግስት፣ የግድግዳ ምሰሶዎች እና ማማዎች፣ ባለ ብዙ ወለል ህንጻ፣ ሀውልቶች እና የኢንዱስትሪ ህንፃ እንደሚገኙባትም ተመራማሪዎች አስረድተዋል።

በውስጡ የሽብልቅ ቅርፅ ያለው የጽሕፈት መደብ የያዙ የሸክላ ዕቃዎች በማከማቻ ክፍል ውስጥ ተሰድረው መገኘታቸውንም አብራርተዋል።

ከዚህ ባለፈም የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁስ፣ ያልተሰበሩ አምስት እንስራዎች እና የተለያዩ መገልገያ መሳሪያዎች መገኘታቸውን ያሆ ኒውስ አስነብቧል።

በእንስራዎቹ ውስጥም በወቅቱ በሸክላ ላይ የተጻፉ መልዕክቶች ደብዘዝ ብለው መገኘታቸውም ተመላክቷል።

በጥንታዊቷ ከተማ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1350 በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት በከፊል መጥፋቷንም አስረድተዋል።

ቦታው በውሃ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በሚያስደንቅ መልኩ በጥሩ ሁኔታ መቆየቱንም ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.