ግብር ከፋዩ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአስተማማኝ መሰረት ላይ በማሳረፍ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ ግብር ከፋዩ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ ጥሪ አቀረቡ።
የገቢዎች ሚኒስቴር ከግብር ከፋዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።
ሚኒስቴሩ በ2014 በጀት አመት 360 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 336 ነጥብ 71 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን የገለጹት ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ÷ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ገቢ ጋር ሲነጻጻር 57 ነጥብ 49 ቢሊየን ብር እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ዓመት ሚኒስቴሩ 450 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ጠቅሰው÷ እቅዱን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ስራዎች ይሰራሉ ነው ያሉት።
መንግስት ግብር ከመሰብሰብ ግብር ከፋዩም ግብር ከመክፈል በተጨማሪ ኢትዮጵያን ለማሳደግ በጋራ ተቀራርበን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲገነባ ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባችሁን ሃላፊነት መወጣት ይኖርባችኋል ነው ያሉት፡፡
የገቢ አሰባሰብ የማያቋርጥ ሀገራዊ ተግባር መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ÷ ያለፈውን ስኬት እያከበርን ድክመቶቻችን በማረም ጠንካራ ጎኖችን ይዘን ለሀገሪቱ ልማትና ብልጽግና ከፍተኛ ድርሻ ያለውን ገቢ ለመሰብሰብ መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የ2014 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀም እና የቀጣይ የ2015 ዓ.ም እቅድ መነሻ ሀሳብ ቀርቦም ሰፋ ያለ ውይይት ይደረጋል ተብሏል፡፡
በአዲሱ ሙሉነህ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!