Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ ህዝብና መንግስት ከሰራዊቱ ጎን በመቆም ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው – የሲዳማ ክልል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ህዝብና መንግስት ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም የሽብር ቡድኑን ህወሓት ወረራ ለመቀልበስ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ፡፡

የሲዳማ ክልል በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ ÷ አሸባሪው ህወሓት በተደጋጋሚ ጊዜ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው ለሦስተኛ ጊዜ በሀገራችን ላይ ጦርነት መክፈቱን አንስቷል።

የሽብር ቡድኑ መንግሥት በተደጋጋሚ አማራጭ የሰላም መንገዶችን ቢያቀርብለትም ድብቅና ስውር አላማው ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ስለሆነ የሰላምና የዕርቅ ጥያቄውን ሊቀበል አለመቻሉን ነው ያስታወቀው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የህወሓትን ሀገር አፍራሽ ተልዕኮ፣ ከፋፋይነት፣ ጥላቻና ነጣጣይነት ዕኩይ ሴራ ጠንቅቆ የተረዳ በመሆኑ ዳግም በሀገራችን ላይ የከፈተውን ጦርነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚቀለብሱትም አጽንኦት ሰጥቷል።

የክልሉ መንግስት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ትዕግስትን ለሚንቅ፣ የሰላም ጥሪን ለማይቀበል፣ የሐገር ሉዓላዊነትን ለሚዳፈር የሀገር አፍራሽ ቡድን ግብአተ መሬቱ እስኪረጋገጥ የሲዳማ ህዝብና የክልሉ መንግስት እንቅልፍ የለውም።

የአሸባሪው ህወሓት መንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን ትተው ለሦስተኛ ጊዜ በሀገራችን ላይ ጦርነት ከፍቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜያት አማራጭ የሰላም መንገዶችን ቢያቀርብለትም ድብቅና ስውር አላማው ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ስለሆነ የሰላምና የዕርቅ ጥያቄዎችን ሊቀበል አልቻለም ።

ህወሓት ሀገር ለማፍረስ ወደ ኋላ የማይል በጥላቻ የታወረ አሸባሪ ቡድን በመሆኑ በሀገራችን ላይ በተደጋጋሚ ጦርነት ከፍቷል ይህም ለሰላም ምንም አይነት ቦታ የሌለው ለሐገርና ለህዝብ ጠንቅ ተልዕኮ እንዳነገበ ያመላክታል ።

ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜ በሀገራችን መንግስትና ንፁሃን ህዝብ ላይ የከፈተው ጦርነት ታሪክ ይቅር የማይለው መጠነ ሰፊ የህይወትና የንብረት ውድመትን አድርሷል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው ዳግም ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነት በመክፈት ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ንቀት አሳይቷል።

ከዚህ ቀደም በከፈተው ጦርነት የትግራይን ህዝብ በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ በመደልልና አልደለል ያለውን በማስገደድ አላስፈላጊ የህይወት መስዋዕትነት እንዲከፍሉ አድርጓል።

ከስህተቱ የማይማረው ህወሓት ዳግም ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የከፈተው ጦርነት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያለውን ጥላቻ ያሳየበት ነው።

ይህም ደግሞ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ እስከ ጫፍ በቁጣ የሚያነሳሳና በተባበረ ክንዳቸው ህወሓትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብኣተ መሬቱ እንዲያፋጥኑ የሚያደረግ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የህወሓትን ሀገር አፍራሽ ተልዕኮ፣ ከፋፋይነት፥፣ጥላቻና ነጣጣይነት ዕኩይ ሴራ ጠንቅቆ የተረዳ በመሆኑ ዳግም በሀገራችን ላይ የከፈተውን ጦርነት በአስተማማኝ ሁኔታ ይቀለብሱታል።

የሲዳማ ህዝብና የክልሉ መንግሥት የአሸባሪውን የህወሓትን ሴራ ጠንቅቆ የሚያውቅ ለ27 አመታት ሲታገል የቆየና ህወሓት ማን እንደሆነ በደንብ የተረዳ ህዝብ በመሆኑ የህወሓት ግባብዓተ መሬት እስኪፈጸም ድረስ የክልሉ ህዝብና መንግሥት ላፍታም ቢሆን እረፍት የለውም።

የሲዳማ ህዝብና መንግስት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ማንኛውንም መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል።

የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ነሐሴ 22/2014 ዓ.ም

ሀዋሳ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.