Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የፍራፍሬ እና ሥጋ ምርቷን ወደ ቻይና የመላክ ዕቅድ እንዳላት ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እንደ ሙዝ፣ አቮካዶ እና ማንጎ ያሉ የፍራፍሬ ምርቶችን እንዲሁም ሥጋ ወደ ቻይና የመላክ ዕቅድ እንዳላት ተገለጸ፡፡

ዕቅዱን ይፋ ያደረጉት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፥ ኢትዮጵያ በቻይና የ“ቤልት ኤንድ ሮድ” ፕሮጀክት አካል በመሆኗ በቻይና ኢንቨስትመንት መጠቀሟን ተናግረዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ለኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መንገድ ዝርጋታ እና ለበርካታ በኢትዮጵያ ውስጥ ለተከናወኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ አነሳሽ ምክንያት እንደሆነም ነው ያመለከቱት፡፡

የፍራፍሬና ሥጋ ምርት ወደ ቻይና የመላክ ውጥን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዘርፉ ከያዟቸው ሠፊ ዕቅዶች መካከል አንዱ መሆኑንም ሰፕላይ ማኔጅመንት የተባለው ድረገፅ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ሥራ በፈረንጆቹ 2018 እንደተጠናቀቀ እና በአሁኑ ጊዜም መስመሩ የሀገሪቷ የጀርባ አጥንት መሆን እንደቻለ ዘገባው ጠቁሟል፡፡

በኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ሥራ መጀመር ኢትዮጵያ ለሎጀስቲክስ ታወጣ የነበረውን 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ማዳን እንዳስቻለም የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብዲ ዘነበን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ቶን የገቢ እና ወጪ ንግድ የጭነት አገልግሎት በ71 ሺህ ኮንቴይነሮች መሥጠት እንደተቻለም ነው የተመለከተው፡፡

98 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ቡናም በዚሁ መስመር ለዓለም ገበያ መቅረቡንም ዘገባው አትቷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.