አሸባሪው ህወሓት መቀሌ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን 12 ቦቴ ነዳጅ መዝረፉን ተመድ ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት መቀሌ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘን 12 ቦቴ ነዳጅ መዝረፉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሪክ ገለፁ።
ቃል አቀባዩ ትናንት ጠዋት ላይ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን በሀይል መቀሌ ወደሚገኘው የድርጅቱ መጋዘን በመግባት 12 የነዳጅ ቦቴዎችን በአጠቃላይ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉን አስታውቀዋል።
በስፍራው የነበሩ የተመድ ሰራተኞችም የሽብር ቡድኑን ዝርፊያ ማስቆም እንዳልቻሉም ነው ያመለከቱት።
ቃል አቀባዩ በህወሓት የተዘረፈው ነዳጅ በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ምግብ ለማቅረብ እና ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የሰብዓዊ እርዳታዎችን ለማድረስ ይውል እንደነበር ጠቁመዋል።
የህወሓት ዝርፊያ የድርጅቱን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ስራውን እንደሚጎዳም ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማናቸውንም የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቆሶች ላይ የሚፈፀም ዝርፊያን እንደሚያወግዝም ገልፀዋል።