ፌዴሬሽኑ ለአፍሪካ ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዝግጅት ላይ የነበሩ አትሌቶችን በተነ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአፍሪካ ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ዝግጅት ካምፕ አስገብቷቸው የነበሩ አትሌቶችን በተነ።
በቶጎ ሎሜ መጋቢት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ሊካሄድ በታቀደው 6ኛው የአፍሪካ ሃገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የሚወዳደሩ አትሌቶችና አሰልጣኞች ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ ሆቴል ገብተው ልምምዳቸውን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ፌዴሬሽኑ አስታውሷል።
የውድድሩ አዘጋጅ የሆነው የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ትናንት ለፌዴሬሽኑ በላከው መልዕክት ውድድሩ ለቀጣዩ አመት መሸጋገሩን አስታውቋል።
ይህን ተከትሎም ልምምድ ላይ የነበሩ አትሌቶችና አሰልጣኞችን ከዛሬ ጀምሮ ፌዴሬሽኑ እንደሚያሰናብት ገልጿል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋትና ፈተና የሆነው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋት ለሻምፒዮናው መራዘም ምክንያት ነው ተብሏል።
ኮንፌዴሬሽኑ ሻምፒዮናው ወደ ቀጣዩ ዓመት መተላለፉን ቢያሳውቅም የሚካሄድበትን ትክክለኛ ወር እና ቀን ግን አልገለጸም።
ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ለቡድኑ አባላት አስፈላጊውን የግብዓትና የሎጅስቲክስ አቅርቦት በማሟላትና ግልፅ ውይይት በማድረግ አትሌቶችና አሰልጣኞቻቸው ያለምንም ችግር ወደየመጡበት እንዲመለሱ እንደሚያደርግም ነው የገለጸው።
በትናንትናው ዕለትም ለልዑካን ቡድኑ አባላት በፌዴሬሽኑ የህክምና ባለሙያዎች አማካይነት ስለኮሮና ቫይረስና ተያያዥ ጉዳዮች አጠቃላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ፥ ከአትሌቶችና አሰልጣኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠቱንም አብራርቷል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision