የአየር ንብረት ለውጥ በዚህ ከቀጠለ የሰው ልጅን ሊያጠፋ እንደሚችል አዲስ ጥናት አመለከተ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ በዚህ ከቀጠለ የሰው ልጅን ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ እንደሚችል አዲስ ጥናት አመለከተ።
የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ካልተቻለ በዚሁ ምክንያት የሰው ልጅ ከምድር ሊጠፋ እንደሚችል መታወቅ አለበት ሲል አዲሱ ጥናት አመልክቷል።
የዘርፉ ሊቃውንት በጥናታቸው ይፋ እንዳደረጉት፥ የአየር ሙቀት ከተገመተው በላይ እየጨመረ ከሄደና ይህንንም መከላከል ካልቻለ እየተፈጠረ ያለው ሁኔታ የአየር ሙቀትና የአየር ንብረት ለውጥ በተፈጥሮ ከሚጠበቀውና በጥናት ከተገመተው በላይ ነው።
ይህ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለም በሰው ልጅ ላይ አሰቃቂ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሚመራው የጥናት ቡድን፥ 10 በመቶ የዓለም ሕዝብን ከማጣት ጀምሮ በምድር ላይ ያለው የሰው ልጅ ከምድረ ገፅ እስከመጥፋት ለሚያደርሱ አስፈሪ ሁኔታዎች ሊጋለጥ ይችላል፥ ይህንም አደጋ ለመከላከል መዘጋጀት ያስፈልጋል ብሏል።
ተመራማሪዎቹ የአየር ሙቀት ከ 5 ነጥብ 4 ዲግሪ ፋራናይት በላይ መጨመር የሚያስከትለው መዘዝ ከቅድመ-ኢንዱስትሪ ዘመን ጋር ሲነጻጸር ቀደም ባሉት ጊዜያት በበቂ ሁኔታ ጥናት እንዳልተደረገበት አንስተዋል፡፡
የበይነመንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ቡድን (IPCC) ባለፈው ዓመት ያቀረበው ሪፖርት፥ የከባቢ አየር የካርበን ልቀት ከቅድመ-ኢንዱስትሪ ዘመን በእጥፍ ቢጨምር እና ፕላኔታችን ግማሽ መንገድ ወደ ፊት የምትሄድ ከሆነ የሙቀት መጠኑ ከ 8 ነጥብ 1 ዲግሪ ፋራናይት በላይ የመጨመር እድሉ 18 በመቶ አካባቢ እንደሆነ ያመላክታል።
የአጥኚ ቡድኑ ሪፖርት እንደሚጠቁመው፥ “የአየር ንብረት ለውጥ የፍጻሜ ጨዋታ አስከፊ ነው። ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ከፍተኛ የአየር ሙቀት፣ ጦርነት እና ተላላፊ በሽታዎች ላይ የሚያተኩር አዲስ ምርምር እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል::
የአየር ሙቀት መጨመር በዓለም ላይ በጣም ለም በሆኑ የግብርና አካባቢዎች የሰብል ምርት ማጣት አደጋን ይጨምራል ሲልም ነው ጥናቱ ያብራራው።
ከዚህም ሌላ የሰዎች እና የእንስሳት መኖሪያዎች እየቀነሱና እየጠፉ ሲሄዱ ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ገዳይ አዳዲስ በሽታዎችን እንደሚያስከትልም ያመላክታል።
የአየር ሙቀት መጨመር ሌሎች የህልውና ስጋቶችን እንደሚያባብስ የጠቆመው ጥናቱ፥ የኢፍትሃዊነት መጨመር፣ የተሳሳተ መረጃ ፍሰት፣ የዲሞክራሲ ውድቀት እና ሌላው ቀርቶ የአዳዲስ አውዳሚ የጦር መሳሪያዎች አስተዳደር ችግርም ያስከትል ይላል።
በሌላ በኩል በቴክኖሎጂ የተራቀቁ ኃያላን ሀገራት በከፋ ጦርነት እርስ በርስ ሊፋለሙ እንደሚችሉ ጠቁሞ፥ ይህም የኅዋ ካርበን እየጨመረ እንዲመጣ ከማድረግም አልፎ፥ የፀሐይ ብርሃንን ለመከላከል እና የሙቀት መጠንን ለመቀነስ ውድ የሆኑ ሙከራዎችን በገንዘብ ለመደገፍ እንደሚገደዱም አመላክቷል፡፡
ምንጭ፡- ስተዲ ፋይንድስ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!