ትጋታችንን ጨምረን፣ አደራችንን ጠብቀን ለላቀ ውጤት ተዘጋጅተናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ትጋታችንን ጨምረን፣ አደራችንን ጠብቀን ለላቀ ውጤት ተዘጋጅተናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለህዝቡ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “አደራችን ትልቅ ቢሆንም፣ ህዝባችንን አስተባብረን ፤ መክሊታችንን እያበዛን ፤ ለላቀ ውጤት መትጋታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
ወይዘሮ አዳነች ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ትጋታችንን ጨምረን ፤ አደራችንን ጠብቀን ለላቀ ውጤት ተዘጋጅተናል!
ሃላፊነት ታላቅ አደራ ነው፡፡ ሃላፊነት ክብርም ፣ እምነትም፣ መመረጥም ነው፡፡
የህዝባችን ችግር ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን እናውቃለን፡፡ በተሰጠን ጊዜና እድል መክሊታችንን መንዝረን አንዳች ነገር ለመጨመር በዓመቱ ላይና ታች ስንል ከርመናል ፤ 24/7 መመሪያችን አድርገን ወጥተናል፣ ወርደናል። ብዙዎችን አስተባብረን፣ አስታዋሽና ተመልካች የሌላቸውን ወገኖች ዝቅ ብለን ተመልክተናል። የበርካታ ዜጎችን ተስፋም አለምልመናል። ከተማችንን ውብና አዲስ ለማድረግም ህዝባችንን አስተባብረን ተግተናል፡፡ ተስፋን ያጫሩ የመለወጥ ዘመናችንን የሚያበስሩ አሻራዎችን አኑረናል፡፡
በጉዟችን ብዙ ብንጨምርም፣ ያጎደልናቸውና ያላሳካናቸው እንዳሉም እናውቃለን፡፡ ከስንዴ መሃል እንክርዳድ አይጠፋምና በሚተጉ መሃከል እምነታቸውን በማጉደል ከአላማቸው ፈቀቅ ያሉና የግል ጥቅማቸውን ያሳደዱ፣ ህዝብን ያስቀየሙም እንደነበር አይተናል። በአጠቃላይ ከህዝባችን የለውጥ ፍላጎትና የኑሮ ሁኔታ አንፃር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅብን በሚገባ እንረዳለን፡፡
በእርግጥ የምናገለግለው ህዝብ ከልካችን በላይ የማይጠይቀን ፤ ስንሰራ ከአንጀቱ የሚመርቀን ፤ ስናለማ የሚያግዘን ፤ስናጎድል የሚገስፀን ፤ ላቅ ሲልም እንደ ወላጅ ሸንቆጥ የሚያደርገን ፤ ለስራ ስንነሳ አንጀቱን አስሮ ከጎናችን የሚቆም ፤ ሚዛናዊ የሆነ ፤ በፍትሃዊነት የሚዳኘን ፤የሚገባንን የሚሰጠን አስተዋይና ታላቅ ህዝብ ነው፡፡
አሁንም ቢሆን ከጥንካሬያችን ተምረን፣ከጉድለታችን ታርመን፣ ክፍተቶቻችንን አስተካክለን መጪውን ዘመን ለበለጠ ውጤት እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡ አደራችንን በላቀ ቁርጠኝነት ለማሳካት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁጭት ተነሳስተናል፡፡ ከህዝባችን መማራችንን ፣ከተግባራችን መቅሰማችን ፣ተባብረን ለላቀ ውጤት መብቃታችን እና የህዝባችንን ተጠቃሚነት ማረጋገጣችንን እንቀጥላለን!!
ህዝባችንም ከመቼውም ጊዜ በላይ ከጎናችን እንደሚቆም እናምናለን!!
አደራችን ትልቅ ቢሆንም፣ ህዝባችንን አስተባብረን ፤ መክሊታችንን እያበዛን ፤ለላቀ ውጤት መትጋታችንን እንቀጥላለን!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!!