ምክር ቤቱ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ምክክር አካሄደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዓለም የጤና ወረርሽኝ በሆነው የኮሮና ቫይረስ ላይ ምክክር አድርጓል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ሁኔታ እና ኢትዮጵያ ቫይረሱ እንዳይገባ እያደረገች ባለው ቅድመ ጥንቃቄ ዙሪያ ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱ አባላትም የኮሮና ቫይረስ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚመለከት በመሆኑ ግንዛቤ ከመፍጠር አንጻር ምን እየተሰራ ነው፤ በሚኒስትሮች ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ እስከ ታች ወርዶ ከክልሎች ጋር ያለው መስተጋብር ምን ይመስላል የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚዋሰኑ ክልሎች ላይ ምን እየተሰራ ነው፤ ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ለቫይረሱ መግባት ሚና ስላላቸው በዚህ ላይ ምን እየተሰራ ነው፤ አሁን የተጀመረው የመከላከል ስራ ፈጣን መሆን አለበት የሚሉ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችም ተነስተዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ የመከላከል ስራው ቅንጅታዊ አሰራር ይፈልጋል መባሉን አስመልክቶ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባከተተ መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ይህን ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት የሆነውን ወረርሽኝ ለመከላከል እስከ ወረዳ ድረስ ትስስር በመፍጠር እየሰራ መሆኑን እና የጤና ሚኒስቴርም ከክልል የጤና ቢሮዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቅዋል።
ከሀገራት ጋር የሚዋሰኑ ክልሎችን አስመልክቶም እስከ 30 የሚደርሱ ኬላዎች ላይ የሙቀት ልየታ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
በበሽታው ዙሪያ ህብረተሰቡን ተደራሽ ለማድረግ በሚዲያዎች አማካኝነት እየተሰራ ነው ያሉት ዶክተር ኤባ፥ ሚዲያ ተደራሽ ላልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም በተለያየ ዘዴዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህ ላይ የምክር ቤት አባላት ከተለያዩ አካባቢዎች ተመርጠው እንደመምጣታቸው የመጡበትን ማህበረሰብ ማሳወቅ ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፥ በሽታውን ለመከላከል እና ከተከሰተም እንደ ሀገር መከላከል ላይ የህክምና ተቋማትን ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የተቋቋመው የብሄራዊ ምክር ቤትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑንም አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ በሽታው ላይ ግንዛቤ እንዲያገኘም እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ፤ ህብረተሰቡ በቀላል ዋጋ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ኬሚካሎችን የሚያገኝበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከመጨባበጥና ከእጅ ንክኪ ጋር ተያይዞ በቫይረሱ የተጠቃ ሰውን ጨብጦ አሊያም በቫይረሱ የተጠቃ ሰው የነካውን ነገር ከነኩ በኋላ አይን እና አፍንጫን መንካት በቀላሉ በቫይረሱ እንድንያዝ ስለሚያደርግ መጨባበጥን መቀነስ እና በየጊዜው በአግባቡ እጅን መታጠብ ተገቢ ነው ብለዋል።