ኢንዶኔዥያዊው ወጣት ከዶሮ እግር ቆዳ ጫማ ሰርቷል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢንዶኔዥያ ባንዱክ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ25 ዓመቱ ኑርማን ፋሪዬካ ከዶሮ እግር ላይ የሚያገኘውን ቆዳ ተጠቅሞ በሚሰራው ጫማ መነጋገሪያ ሆኗል።
ወጣቱ አባቱ የዶሮ እግር ቆዳን አጠቃላይ ሁኔታ በመመርመር ጫማ መስራቱን እንዲሞክረው ምክረ ሃሳብ አቅርበውለታል።
እርሱም የአባቱን ምክረ ሃሳብ በመቀበል በፈረንጆቹ 2017 ለመጀመሪያ ጊዜ ከዶሮ እግር ቆዳ ጫማ መስራቱን አስታውሷል።
የዶሮ እግር ቆዳ ከእባብ ወይም አዞ ቆዳ ጋር ተመሳሳይና የሻካራነት ባህሪ እንዳለው ተጠቁሟል።
አሁን ላይ ፋሪዬካና አባቱን ጨምሮ አምስት አባላት ይህን ስራ እየሰሩ ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ አልያም በከፊል ከዶሮ እግር ቆዳ ጫማዎችን እያዘጋጁ ይገኛል።
አንድ ጥንድ ጫማን ለማምረትም 45 ዶሮን እንደሚጠቀሙም ገልጸዋል፤ ጫማው ገበያ ላይ ከ35 እስከ 140 ዶላር ዋጋ ያወጣል ተብሏል።
አሁን እየሰሩ ያሉት ጫማም በደንበኞች ዘንድ መወደዱንም ወጣቱ ገልጿል።
ምንጭ፦ ሬውተርስ