የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ የህክምና ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል የቆየውን የሚሊኒየም አዳራሽ ከምስጋና ጋር ለባለቤቱ መለሰ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር ላለፉት ሁለት ዓመታት የኮቪድ የህክምና እና የድንገተኛ ምላሽ ማዕከል ሆኖ ሲያገለግል የቆየውን አዲስ ፓርክ /የሚሊኒየም አዳራሽ/ ከምስጋና ጋር ለባለቤቱ ለሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አስረከበ።
የጤና ሚኒሰቴር ሚኒስትር ዶከተር ሊያ ታደሰ ማዕከሉን ለሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባስረከቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት የኮቪድ -19 ወረርሽኝን ለመከላከል ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፈን፥ እያስከተለ ያለውን ችግር በመቋቋም ለዚህ ዕለት በመብቃታችንና የሚሊኒየም የህክምና ማዕከልን መልሰን ማስረከብ በመቻላችን ደስተኞች ነን ብለዋል።
ወረርሽኙ በከፋበት ወቅት ለብሄራዊ ኮሚቴው ቀርቦ ለነበረው አዲስ ፓርክን ለኮቪድ 19 የህክምና ማዕከልነት የመጠቀም ጥያቄ አዲስ ፓርክ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ላሳዩት ቀና ትብብር ምስጋና አቅርበዋል።
በስምንት ሳምንታት ዝግጅት አዳራሾቹን ወደ ሆስፒታልነት በመቀየርና ግብዓቶችን በማሟላት ስራ ተጀምሮ ብዙዎች እንዲፈወሱበት ማድረግ መቻሉን የገለፁት ሚኒስትሯ÷ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ ስራውን በኃላፊነት በመረከብና ሌሎችን በማስተባበር ላከናወነው ውጤታማ ስራ አመስግነዋል።
ዛሬ የኮቪድ-19 የህክምና እና የድንገተኛ ምላሽ ማዕከሉን ዘግተን ወደነበረበት የምንመልሰው ኮቪድ ስለጠፋ ሳይሆን አገልግሎቱን በሌሎች የጤና ተቋማት ለማቅረብ የምንችልበት አቅም ስለፈጠርንና በመላ ሀገሪቱ የክትባት ሽፋንን በማድረስና የበሽታውን ጉዳት መቀነስ በመቻሉ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ክትባቱን ያልወሰዱ የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲወስዱና ጥንቃቄያቸውን ሳይዘናጉ እንዲተገብሩ ማድረግ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው÷ተቋሙ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 120 ሚሊየን ብር ለአዲስ አበባ መስተዳድር እና የሚሊኒየም አዳራሽን ለጤና ሚኒስቴር በነፃ እንደሰጠ ሁሉ በቀጣይም ለህዝብ ጥያቄዎች የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።