ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጀነራል አል ቡርሐን ጋር በናይሮቢ ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጀነራል አዱልፈታህ አል ቡርሐን ጋር በናይሮቢ ተወያዩ።
ለኢጋድ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ናይሮቢ የሚገኙት መሪዎቹ፥ ከጉባኤው ጎን ለጎን በወቅታዊ ቀጣናዊ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
ውይይቱን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ሁለቱ ሀገራት በሰላማዊ መንገድ ሊሠሩባቸው የሚችሉ በርካታ የትብብር መሠረቶች እንዳሏቸው አረጋግጠናል” ብለዋል።
“ያለን ትሥሥር ከየትኛውም መከፋፈል የሚበልጥ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ሁለታችንም ያልተፈቱ ቀዳሚ ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ቁርጠኝነታችንን ገልጸናል” ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በ39ኛው የኢጋድ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ነበር ኬንያ፣ ናይሮቢ የገቡት።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!