የቻይና ኩባንያ ጭምብል ያደረጉ ሰዎችን ማንነት የሚለይ ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቻይና ኩባንያ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ያደረጉ ሰወች ማንነት መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፋ አድርጓል።
ቴክኖሎጂው ዓለምን እያስጨነቀ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ለመዋጋት እገዛ እንደሚያደርግ ታምኖበታል።
ሃንቮን በተባለው ኩባንያ የተዋወቀው ቴክኖሎጂ ሰዎችን ጭምብል ሳያወልቁ ማንነታቸውን መለየት የሚያስችል ነው ተብሏል።
በተጨማሪም ከሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ጋር ከተገናኘ በኋላ ከ38 ዲግሪ ሴሊሺየስ በላይ የሰውነት ሙቀት ያላቸውን ሰዎች መለየት እንደሚችልም ነው የኩባንያው ምክትል ፕሬዚዳንት ሁዋንግ ሊ የተናገሩት።
ከዚህ ባለፈም የወንጀል ተጠርጣሪዎች፣ አሸባሪዎች ወይም የተለያየ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውን ግለሰቦች መለየት እንደሚችልም ተነግሯል።
ቴክኖሎጂው 30 ያክል ሰወችን በሰከንድ የሚለይ ሲሆን፥ 6 ሚሊየን የሚጠጉ ጭምብል ያደረጉ እና ያላደረጉ ሰወችን ለጥናታቸው መጠቀማቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ጭምብል ያደረጉ ሰወችን የመለየት አቅሙ 95 በመቶ ሲሆን፥ 99 ነጥብ 5 በመቶ ደግሞ ጭምብል ያላደረጉ ሰዎችን የመለየት አቅም አለው ነው የተባለው።
በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ዓለም ላይ መስፋፋቱን ተከትሎ የፊት ጭምብል መጠቀም የግድ ሲሆን ቴክኖሎጂውን ከቻይና በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠቀም ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑም ነው የተነገረው።
ምንጭ፦ ሬውተርስ