Fana: At a Speed of Life!

አስቸጋሪ ፈተናዎችን በጋራ በመሻገር ዘላቂ ሰላምን እና ልማት ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረት እንቀጥላለን – አቶ መለሰ ዓለሙ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አስቸጋሪ ፈተናዎችን ሁሉ ከህዝባችን ጋር በጋራ በመሻገር ዘላቂ ሰላምን እና ልማት ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለስ ዓለሙ ገለጹ ፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ “አሻራችን ለትውልዳችን!” በሚል 4ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
መርሐ ግብሩ በአሸባሪው ሸኔ ለተጨፈጨፉ ንጹሃን ዜጎች የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረ ሲሆን፥ በአሸባሪዎች ለተጨፈጨፉት ንፁሃን ሀዘናችንን እየገለጽን፥ ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ ከህዝቡ ጋር እያደረግነው ከምንገኘው ርብርብ ለአፍታም እንደማንዘናጋ ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ አቶ መለስ ተናግረዋል ፡፡
ኢትዮጵያ ከድህነት ለመቆራረጥ የጀመረችውን የብልፅግና ጎዳና የማይፈልጉ ኃይሎች በንፁሃን ላይ የሽብር ድርጊት እየፈፀሙ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፥ ፈተናዎችን ሁሉ ከህዝባችን ጋር በመሻገር ለቀጣዩ ትውልድ የበለፀገችና አረንጓዴ የለበሰች አገር እናወርሳለን ብለዋል።
በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በተሰየመው መንገድ አካፋይ ላይ በዛሬው ዕለት የተተከሉት ችግኞች ለከተማዋ ውበት ብቻ ሳይሆኑ እስትንፋስም መሆናቸውን ጠቁመው ፥ መትከል ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት መንከባከብም ከሁሉም አካላት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ነፃነት ዳባ በበኩላቸው÷ ወቅቱ በተባበረ ክንዳችን ችግኝ የምንተክልበት፣ ሰላም የምናረጋግጥበትና ልማትን የምናፋጥንበት መሆኑን ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት አባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎችም ችግኝ መትከልን ጨምሮ በሌሎችም የልማትና የሰላም ማስከበር ስራዎች ሁሉም ዜጋ በአንድነት እንዲረባረብ ጥሪ ማቅረባቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.