Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ የፈረንሳይ ባለሐብቶች የገበያ ዕድል እና ማበረታቻዎች እንደተመቻቹ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ሻውል መዋዕለ-ንዋያቸውን በኢትዮጵያ ማፍሰስ ለሚፈልጉ የፈረንሳይ ባለሐብቶች የገበያ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ምቹ የሥራ ምኅዳር እንደሚጠብቃቸው ገለጹ፡፡

በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ሻውል የኢትዮ-ፈረንሳይን የ125 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሠረተበትን በዓል ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ከሚሰሩ የፈረንሳይ ባለሐብቶች ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይታቸው የፈረንሳይ ባለሐብቶች በተለይ በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ በማምረቻ፣ በማዕድን ፣ በቱሪዝም እና ቴክኖሎጂን በመሳሰሉ ዘርፎች ላይ ቢሰማሩ ድጋፍ እንደሚመቻችላቸው አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ115 ሚሊየን በላይ ህዝብ እና በፍጥነት እያደገ የሚገኝ ኢኮኖሚ እንዳላት ለባለሐብቶቹ ተገልጿል፡፡

አምባሳደር ሄኖክ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በፈረንሳይ ድጋፍ የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መሥመር ዝርጋታ ዕውን እንደሆነ እና ከዛን ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንትና የንግድ ፍሰት እንደተሳለጠ አስታውሰዋል።

ፈረንሳይ ካናል ፕላስ እና ሾፍሌት በተሰኙ ኩባንያዎቿ በኢትዮጵያ ተሰማርታ ኢኮኖሚው ላይ መነቃቃት እንደፈጠረችና ለዜጎችም ሥራ በመፍጠር ረገድም አስተዋጽዖ እንዳበረከተች ነው የተናገሩት፡፡

ፈረንሳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን መንግስት የሪፎርም አጀንዳ በተለይም በባሕል ላይ እየሰሩ የሚገኘውን ፕሮጀክት በመደገፍ ረገድም ላበረከተችው አስተዋፅዖ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡

በቢዝነስ ፎረሙ ላይ በግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ፣ በቱሪዝም፣ በማምረቻ፣ በቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ ፣ በኢንዱስትሪዎች እና በበረራ ላይ የተሰማሩ 30 የሚደርሱ ከፈረንሳይ የተውጣጡ ኩባንያዎች እና ተወካዮች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ደግሞ 15 በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.