የአዲስ አበባ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 4ኛው ዙር የአዲስ አበባ ከተማ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጀመረ።
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር ኤርጎጌ ተስፋዬ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ፣ እንዲሁም የፌደራል እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ አርበኞች ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት መርሃ ግብሩ በይፋ ተጀምሯል።
በ4ኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ 11 ሚሊየን የተለያዪ ችግኞች መዘጋጀታቸው በመርሃ ግብሩ ተገልጿል።
የአዲስ አበባን የአየር ሁኔታ ለማሻሻልና ለዜጎችም የምትመች ከተማ ለማድረግም የአረኝጓዴ አሻራን ማኖር ይገባል ተብሏል ።
የተለያዩ ሀገር በቀል እፅዋትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች የሚተከሉ ሲሆን፥ በአጠቃላይ 40 በመቶ ችግኞች የውበት፣ 40 በመቶ የጥላ እንዲሁም 20 በመቶ ደግሞ ምግብ ነክ ናቸው።
የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ባለፈዉ ሳምንት መጀመሩ ይታወቃል።
በዓለምሰገድ አሳዬ