Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)  ከሳዑዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ እስካሁን ድረስ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎችን መመለስ መቻሉን ይፋ አደረገ።

 

16 የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ያካተተው ብሔራዊ ኮሚቴ ባለፉት ወራት በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን ለማስመለስ በተደረገው ጥረት ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

 

ስብሰባውን የመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሲራጅ ረሽድ እንደተናገሩት፥ እስካሁን 111 ጊዜ በተደረጉ በረራዎች ከ40 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል ነው ያሉት።

 

አምባሳደሩ 102 ሺህ ዜጎችን ለማስመለስ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር እስከ አውሮፓውያኑ ሰኔ 22 ድረስ ማሳካት የተቻለው 40 በመቶ እንደሆነ ገልጸዋል።

 

በቀጣይም ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም በተቻለ ቅንጅታዊ አሰራር የታቀደውን ግብ ለማሳካት በትብብር መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተነስቷል።

 

ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በችግር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ራሱን በቻለ የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑ በውይይቱ ተጠቅሷል።

 

በውይይቱ ላይ በብሔራዊ ኮሚቴው የተካተቱ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.