Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዓለም ዓቀፉን የሴቶች ቀን በማስመልከት ያስተላለፉት መልዕክት

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 29 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ዓለም ዓቀፉን የሴቶች ቀን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን እንደ ሌሎች ሀገራት ሁሉ በዛሬው ዕለት እያከበርን ነን፡፡
 
ይህንን ዓመት ልዩ የሚያደርገው የቤጂንግ የስምምነት መርሀ ግብር 25ኛ ዓመት፤ ሴቶች በሰላምና ጸጥታ ላይ እንዲሳተፉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ 1325 20ኛ ዓመት ፤ የሴቶች አስርተ ዓመት ብሎ የአፍሪካ ህብረት ያሳለፈው ውሳኔ የሚገባበደድበት መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም መለስ ብለን የመጣንበትን ጎዳና እንድንመለከት ያስገድደናል፡፡
 
በሀገራችን በሴቶች ጉዳይ ላይ የታየው ዕድገት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው ፡፡ የእኔም እዚህ ቦታ ላይ መገኘት የዚህ ቀጥተኛ ውጤት ነው፡፡ በተመሳሳይ ደረጃ በአፍሪካም እየታዩ ያሉ ግኝቶች ተስፋ የሚሰጡ ናቸው፡፡
 
ይሁንና ሴቶችን በማብቃትና እኩልነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ ሥራው ተጠናቋል ብለን የምናስብ ከሆነ ተሳስተናል ፡፡ ሥራው ገና ተጀመረ እንጂ፡፡
 
እውነት እንነጋገር ካልን ደግሞ ከፍተኛ ውጤቶች የተገኙ ቢሆንም በዓለም ደረጃ ለሴቶችና ሴት ልጆች የተገባውን ቃል በመተግበር ረገድ ብዙ ይቀረናል ፡፡
 
ለእነርሱ ትምህርት ባለመዳረሱ በርካታ ምርጥ ጭንቅላቶችን አጥተናል፡፡ የጾታ ጥቃትን ባለመከላከላችን ፤ የጾታ እኩልነት ተዛብቶ በመቅረቱ ፤ ከጥቂቶች በስተቀር ለምርጫ ባለመቅረባቸው ወይንም ባለመመረጣቸው ብዙ ለማደግ አልቻልንም፡፡ ዘላቂ መፍትሄ በማስገኘት ረገድ የሴቶች ጉዳይ በቂ ትኩረት አላገኘም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
 
ሀገራችን ባለፈው ዓመት ብዙ ስኬቶችን አስመዝግባለች፡፡ሴቶች ወደ ሃላፊነት ቦታ መጥተዋል ፡፡ በአግባቡ ሊከበርም ይገባል፡፡ቀላል ግኝት አይደለምና፡፡
 
ለሴቶች የመልካም አጋጣሚ በር ሲከፈትልን እንዳይዘጋና ሌሎችም ሴቶች እንዲያልፉበት ፤ ጥቂቶች ላይ የበራውን መብራት ሌሎችንም እንዲያጥለቀልቃቸው ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡
 
ለዚህም ነው ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን ማርች 8ዓመት እየጠበቅን ማክበር ብዙ የቤት ስራ ላለብን ሰዎች በቂ የማይሆነው ፡፡የሴቶች ጉዳይ በዓመት 365 ቀናት የሚሰራበት መሆን አለበት፡፡ ስናከብረውም ስኬቶቻችንና እጥረቶቻችንን የምንመዝንበት ፤ ለመጪው ዓመት ቁርጠኝነታችንን አሳድገን የምንጓዝበት መሆን ይገባዋል፡፡
 
ወጣት ሴቶች ግረው ጥረው ፤ ቤተሰቦቻቸውንና ራሳቸው ተጎድተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቀው እንደምንም ዩንቨርስቲ ከገቡ በኋላ እንዲመረቁ ማድረግ ቀዳሚ ተግባር ነው ፡፡ እውነታው የሚያሳየን ግን በርካታ የሆኑት ብዙም ሳይቆዩ እንደሚባረሩ ነው ፡፡ ሴትን ለማስተማር ካልቻልን ፤ ጤናማና አምራች ካላደረግናት ስለ እኩልነት ማለማችን ብዙም ትርጉም የለውም፡፡ ለሴት የነጻነቷ ቁልፍ ትምህርት ነው፡፡
 
ዘንድሮ ጥረት ተደርጎና በልዩ ድጋፍ በርካታ ሴቶች ዩንቨርስቲ ቢገቡም በመጀመሪያ መንፈቀ ዓመት የታየው ውጤት የሚያሳስብ ነው ፡፡ በዚህ ረገድ #ለእህቴ በሚል መሪ ቃል ሴት ባለሀብቶች ባደረጉት ድጋፍ ተጋላጭና ውጤታቸው ደካማ ለሆኑ ሴት ተማሪዎች (ለተወሰኑ ወንዶችም ጭምር) የተጨማሪ ትምህርት ፕሮግራም (ቲቶሪያል) ለጊዜውም ቢሆን በስድስት ዩንቨርስቲዎች ተጀምሯል፡፡ ከተረባረብን በሁሉም ዩንቨርስቲዎች የማናደርግበት ምክንያት የለም፡፡እህቶቻችንን ለበጎ ተግባራቸው ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
 
ተፈጥሮ ለሴቶች የሰጣቸው ከፍተኛ ጸጋ ትውልድን ማቆየት ነው:: ለዚህም የሚያበቃቸው ተፈጥሯዊ ሂደት በወር አበባ ይጀምራል:: ዛሬ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ስለሌላቸው ፤ በአመቺ ቦታ እጥረት በርካታ ተማሪዎች በወር እስከ አንድ ሳምንት ድረስ ከትምህርታቸው
 
ይስተጓጎላሉ፡፡ እንደነዚህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጀግና የሚያሰኛቸውን ሥራ የሚያከናውኑ ኢትዮጽያዊት ወ/ሮ ፍሬወይኒ መብራህቱ እንዳሉ የነገረን CNN ነው!!
ይህ ጉዳይ በዚህ ደረጃ ከወጣ ፤ መብራት ከበራበት ፤ ወደ ሗላ መመለስ የለበትም በማለት ብሔራዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሟል::
 
በበጎ ፈቃደኝነት አባል የሆኑትን፤ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት ልዩ ልዩ የንጽህና መጠበቂያ በማምረት፤ በማደል፤የተሠማሩትን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ:: ይህ ንቅናቄ ያቀናጃል፤ ያሳድጋል እንጂ ሌሎች ጥረቶችን አይገታም:: አገራችን እያደገች ስትመጣ ሴት ተማሪዎችን ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ የንጽህና መጠበቂያ በነጻ የሚያገኙበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ አለኝ:: በዚህ ረገድ በእህቴ ፕሮግራም አማካኝነት ለብዙ ጊዜ የሚያገለግል የንጽህና መጠበቂያ ማምረቻዎችን ለመትከል እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ይህንን ችግር ተሸክመን ስለ እኩልነት ማውራት ያስቸግራልና::
 
የትምህርት ሰነዶችን ፎቶ ኮፒ ለማድረግ አቅም የሌላቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥቂት አይደሉም:: በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን ላይ እያለን ሳተላይት አምጥቀን ስናበቃ… ይህንን ችግር ታሪክ ለማድረግ ልንነሳሳ ይገባል :: ወረቀት በታብሌት ቢተካስ ? በአገራችን የታሰበው የታብሌት ምርት ብናሳድገውስ?ከፍ ብለን እንዳናልም የሚከለክለን የለም፡፡
 
በዚህ አጋጣሚ ማንም ሳያውቃቸው፤ ሳይወራላቸው በየሆስፒታሉ በሽተኞችን ፤አረጋውያንን፤ ጎዳና ተዳዳሪዎችን… የሚደግፋ፤ሴት ሰራ ፈጣሪዎችን ለማብዛት የሚደክሙ በርካታ ወገኖቻችንን፤ሴቶችን ለማመስገን እወዳለሁ:: ላበረታታቸውም እፈልጋለሁ፡፡ሌሎችም የእነርሱን ፈልግ እንዲከተሉ እጋብዛለሁ፡፡
 
ዛሬ በግብርና ክላስተር ላይ እየተሳተፉ ያሉ ሴት ገበሬዎችን በማዳመጥ ብቻ ተስፋ እንዳለን ይታያል፡፡ በገጠር እንዲሁም በከተማ ይፋዊ ባልሆነ የኢኮኖሚዘርፎች ላይ የምትገኘውን ሴት ከደገፍናት ቀጥታ እርሷ ላይ ደርሰን መሰረታዊ ጉዳዮችን ብናስጨብጣት እርሷን ብቻ ሳይሆን መላ ቤተሰብን፤ ማህበረሰብን ለመለወጥ ይቻላል፡፡ ስለሆነም የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን በቀጥታ ልንደርሳቸው እንችላለን፤እንበርታበት፡፡
 
እዚህ ላይ የደረስነው እናቶቻችንና አባቶቻችን ባቆዩልን እሴት ነው፡፡ እዚህ ከፍተኛ ድል ላይ ለመድረስ እድል ያገኘነው በጀግና እናቶችና አባቶች ትከሻ ላይ በመቆማችን ነው፡፡ አንዳችን ለአንዳችን መሰላል እንሁን፤ እንደጋገፍ፤ እንረዳዳ፡፡ ለማንኛውም ጥረታችን መሠረታዊ ቁልፍ መተባበራችን ፤ በጋራ መቆማችን ነው፡፡
 
የሴቶች ጥያቄ የሴቶች ጉዳይ ነው፤ሴቶች በራሳቸው ይወጡት፤ለችግሮቻቸው መፍትሄ ማስገኘት ያለባቸው እነርሱ ናቸው….ከሚል አስተሳሰብ መላቀቅ አለብን፡፡ ሃላፊነትን መሸሽ ይሆናልና፡፡ይህ ቀን የሁላችንም ነው፡፡
 
መጪው ዓመት የተግባር እናድርገው፡፡
 
ኢትዮጵያ ሀገራችን ብሩህ ተስፋ ያላት ታላቅ ሀገር ነች፡፡
 
ሴቶች ትልቅ ቦታና ድርሻ አለን ፤የበኩላችንን አብረን እንወጣ፡፡
መልካም ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.