አማራ ባንክ በዛሬው ዕለት ተመርቆ ሥራውን በይፋ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር በዛሬው ዕለት ተመርቆ ሥራውን በይፋ ጀምሯል።
የአማራ ባንክ አክሲዮን ማህበር የምረቃ እና ስራ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት በዛሬው ዕለት ለገሃር በሚገኘው የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ተካሂዷል።
በምረቃ ስነ ስርዓቱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፣ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አማራ ባንክ በዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ተመርቆ በ72 ቅርንጫፎቹ በይፋ ስራ መጀመሩ በስነ ሰርዓቱ ላይ ተገልጿል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ለባንኩ አደራጆች እና መስራቾች እንዲሁም ባንኩ ዕውን እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከአገሪቱ ለውጥ ጋር ተያይዞ ባንኩ በፋይናንሱ ዘርፍ ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ተሞኮሮዎችን ቀምሮ የተሻለ ስራ እንደሚሰራ እምነቴ ነው ብለዋል።
ባንኩ ሁሉን አካታች እና ተወዳዳሪ በመሆን የዜጎችን ብሎሞ የአገሪቱን ልማት በማፋጠን ረገድ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም ነው የተናገሩት።
የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ አማራ ባንክ ለአንድ ዓመት ከሦስት ወር ባደረገው የአክሲዮን ሽያጭ 185 ሺህ ባለ አክሲዮኖችን ማፍራቱን ተናግረዋል።
በዚህም በ6 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የተፈረመና 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሄኖክ ከበደ በበኩላቸው፥ አማራ ባንክ የተቀናጁ ሀሳቦች እና የተባበሩ እጆች የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውጤት ሆነው የተመሰረተ ባንክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባንኩን እውን ለማድረግ እና ሥራ ለማስጀመር ውጣ ውረድ እንደነበረ ገልፀው፥ ተቋሙ የታለመለትን ዓለማ ከግብ ያደርስ ዘንድ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡
የተቀመሩትን የባንኩን እሴቶች በማጉላት በፋይናስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ባንኩ ቃሉን ከተግባር ጋር የተገናኘ እንዲሆን በሙሉ ልብ ገበያውን በመቀላቀል የኢንዱስትሪ ጉልበት ለመሆን እንሠራለን ብለዋል፡፡
ሀገሪቱ የጀመረችውን ልማት ለማፋጠንም ከቀደሙ ባንኮች ልምዶችን በመውሰድ፣ ዘመኑን የዋጁ የባንክ ስርዓቶችን ቀምሮ በመተግበር በዘርፉ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የተሸለ እና ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት በቅንጅት እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ