በሐረሪ ክልል የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ ገለጹ።
የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በክልሉ የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ በየዘርፉ የተቋቋሙ የተለያዩ ግብረኃይሎች በ60 ቀናት ያከናወኗቸውን ተግባራት ገምግሟል፡፡
በመድረኩ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሀመድ እንደገለጹት÷ የሕዝብን ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት አንፃር በየዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ተግባራትን ማጠናከር ይገባል።
በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የሕዝብ እንግልት ከማስቀረት አንፃር ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በማይወጡ አመራሮች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው የገለጹት፡፡
በቀጣይም እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን በማጠናከር፣ ፕሮጀክቶች እንዳይጠናቀቁ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት እና በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን በተመለከተ÷ በጥቅም በመተሳሰር ሕዝቡ እንዲማረር የሚያደርጉ አካላትን መታገልና አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ቅንጅታዊ አሠራሮችን ማጎልበትና በየተቋማቱ የሚከናወኑ ተግባራት በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ ማድረግ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ዘርፉን በአግባቡ መደገፍ እንደሚገባም ነው የተገለጸው፡፡
በውይይቱ የተለያዩ ተቋማት የስራ ሀላፊዎችና ተወካዮች የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች እና የሚመለከታቸው አካላት መገኘታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!