በአማራ ክልል የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የመፈጸም አቅም ማደግ እንዳለበት ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በክልሉ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የመፈጸም አቅምን በማሳደግ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኘውን የታችኛው ርብ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የሥራ አፈጻጸም ተመልክተዋል።
የታችኛው ርብ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ግንባታው ሲጠናቀቅ 3 ሺህ 100 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እንደሚያስችል ተገልጿል።
አሁን ላይ ቀሪ ሥራዎችን በ16 ወራት አጠናቆ ለማስረከብ ውል ወስዶ የሚሠራው ሀገር በቀሉ ዓባይ ኮንስትራክሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሆኑ ተጠቁሟል።
ሥራውን የካቲት 2013 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም የማስረከቢያ ጊዜ እንዲሆን ውል ተወስዷል።
ይሁን እንጂ አሁናዊ የሥራ አፈጻጸሙ ገና 21 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ነው የሳይት ተቆጣጣሪው ኢንጅነር ታገሰ ዓለማየሁ የተናገሩት።
እንደ ኢንጅነር ታገሰ ገለጻ÷ለፕሮጀክቱ መዘግየት ምክንያት የመጀመሪያው ካሳ የተከፈላቸው አርሶ አደሮች በጊዜ አለመነሳት ነው።
ውል ወስዶ ግንባታውን የሚሠራው ተቋራጭ አቅም ውስንነትም የመዘግየቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ችግሩን ያዩት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የመስኖ ፕሮጀክቱ ችግሮች ተፈተው በቀጣይ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የርብ መስኖ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎችንም ፕሮጀክቶች በጊዜ በማጠናቀቅ የአማራ ክልልን የመስኖ ልማት ሽፋን ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ዶክተር ይልቃል ተናግረዋል።
ከመስኖ ግድቦች በተጨማሪም አነስተኛ የወንዝ ውኃ መጥለፊያ የፓንፕ ጀነሬተሮችን በመግዛት ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት የክልሉ መንግሥት እቅድ እንደያዘ መግለጻቸውንም አሚኮ ዘግቧል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ በአማራ ክልል የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ የማጠናቀቅ አቅምን በማሳደግ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የተለያዩ የክልልና የዞኑ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።