የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እድሳትና የዓድዋ 00 ፕሮጀክቶችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ግንቦት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እድሳትና የዓድዋ 00 ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።
ፕሮጀክቶቹን ያስጎበኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በጉብኝቱ ወቅት፥ “ምክር ቤቱ የመዲናዋን የለውጥ እንቅስቃሴን ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የብልጽግና ጉዟችንን ለማሳለጥ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሃሳብ አፍላቂነትና የተግባር አመራር ሰጪነት በሁሉም ረገድ የምናከናውናቸውን የልማት ስራዎች እየተከታተለ እንዲደግፈንና ማስተካከል የሚጠበቅብንን ጉዳዮች በማመላከት የበኩሉን አሻራ እንዲያኖር እንፈልጋለን” ብለዋል ።
“ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች ስንል በእነዚህ ተጨባጭ የልማት ስራዎቻችን ነው” ያሉት ከንቲባ አዳነች፥ “ሩቅ ማለም ወይንም አርቆ መመልከት የሚል ስያሜ የሰጠነው ከማዘጋጃ ቤት እስከ ለገሀር ያለው የጎዳና ማስዋብ ሥራ፣ በቀላሉ የምንጓዝበትን አዲስ እይታ ፍንትው አድርጎ እንዲያስመለክት ተደርጎ የተገነባ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የከተማዋን የወደፊት ዕድገትና ተስፋ የማይመጥን ነበር ያሉት ከንቲባዋ፥ ዛሬ ላይ ከማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ በተከናወነ የአካባቢ ገጽታን የማስዋብ ስራዎች ዜጎች ሲያሻቸው የሚናፈሱበትና የሚያነቡበት ሥፍራ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
የዓድዋን ታሪክ እዚህ ቦታ ሕያው አድርገን ለማስቀም እንዲቻል ገድሉን ሕያው አድርገው የሚያሳዩ ማስረጃዎቻችንን የዘርፉ ሙሁራን እያሰባሰቡ እንደሚገኙና የፓርኩ ዲዛይን የአባቶቻችንን የዓድዋ ተራራ ውጣ ውረድ እንዲያሳይ ተደርጎ እየተገነባ ያለ መሆኑን ማብራራታቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።