“በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚታይ ለውጥ ለማምጣት የፓርላማ አባላት ሚና የላቀ ነው”- አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢኮኖሚ ዘርፍ የሚታይ ለውጥ ለማምጣት የምክር ቤት አባላት ሚና የላቀ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ተናገሩ።
አፈ-ጉባዔው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት የ10 ዓመቱን የልማት መሪ ዕቅድ ላይ በተወያዩበት ወቅት፥ በኢኮኖሚው ዘርፍ የሚታይ ለውጥ ለማምጣት የምክር ቤት አባላት ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ከኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ የሕዝብን ጥያቄ በማይፈቱ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤት አመራሮች ላይ ከተጠያቂነት ባሻገር ከስልጣን የማስወገድ ርምጃ ጭምር የሚወሰድ መሆኑንም አፈጉ ጉባዔ ታገሠ አስገንዝበዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ እቅዱን ባቀረቡበት ጊዜ እንደተናገሩት÷
በ10 ዓመቱ የልማት ፍኖተ-ካርታ መርህ መሠረት ትልቁ ትኩረት የተሰጠው ለግብርናው ዘርፍ ሲሆን፤ ይህም ውሃን እና መሬትን ማገናኘት ነው ብለዋል፡፡
በአንፃሩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከገጠሙት ተግዳሮቶች መካከል የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የዋጋ ግሽበት፣ ሥራ አጥነት፣ ሌብነት ፣ የልማት ፕሮጄክቶች የአፈጻጸም ጉድለት፣ የፀጥታ እና የልማት አጋሮች የፋይናንስ ፍሰት መስተጓጎል ተጠቃሽ ስመሆናቸውን ክብርት ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡
የ10 ዓመቱ ፍኖተ-ካርታ ስኬታማ እንዲሆን በክትትል እና ቁጥጥር ሥራው የፖለቲካ ውሳኔ የሚሹ ሥራዎች የማስተካከያ እርምት እንዲደረግባቸው በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡
እንዲሁም ለኢኮኖሚው ዕድገት ማነቆ የሆኑ የፖሊሲ፣ የአዋጅ፣ የደንብ እና የመመሪያ ተግዳሮቶች እንዲሻሻሉ በማድረግ በኩል የምክር ቤቱ ሚና የላቀ እንደሆነ በዝርዝር ማብራሪያው ወቅት ተጠቁሟል፡፡
በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ መሠረት የሀገሪቱ ዜጎች እኩል እና ፍትሓዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ታሳቢ መደረግ እንዳለበት የጠቆሙት የምክር ቤቱ አባላት፥ የሕዝብን ጥያቄ በአግባቡ በማይፈታ አመራር ርምጃ ሊወሰድበት ይገባል ብለዋል፡፡
ፈታኙን የኑሮ ውድነት ለመግታትም አስፈላጊው ርብርብ መደረግ እንዳለበት ነው የምክር ቤቱ አባላት ያሳሰቡት፡፡
በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ቁርጠኛ አቋም መያዝ እንዳለበት የተጠቆመ ሲሆን፥ አሁን የሚስተዋለው የግብዓት አቅርቦት ችግር በሚቀጥሉት ዓመታትም ተግዳሮት ሆኖ እንዳይቀጥልና የዕቅዱ አፈጻጸም እንዳይቀለብስ ፥ ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ በውይይቱ መነሳቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!