የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የሀገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ብቸኛው መፍትሄ የህግ የበላይነትን ማስከበር መሆኑን መንግስት ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የሀገርን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ብቸኛው መፍትሄ የህግ የበላይነትን ማስከበር መሆኑን መንግስት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፥ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚታየውን ህገወጥነትና የሰላም መደፍረስ እንዲሁም ስርዓት አልበኝነትን መንግስት እንዲቆጣጠር ህዝቡ በተደጋጋሚ በአንድ ድምፅ ሊባል በሚችል መልኩ ሲጠይቅ መቆየቱን አንስቷል።
ከሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ውስጥ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ የዚሁ አካል መሆኑን ነው ያስታወቀው።
በሁሉም ክልሎች እየተካሄደ በሚገኘው ኦፕሬሽን በርካታ ግለሰቦችና ቡድኖች ከነትጥቆቻቸዉ፣ ከዘረፉት ንብረትና ቀጣይ ሊፈፅሙ ያቀዷቸዉ ጥፋቶችን ካሰፈሩባቸው ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ስር እንዲዉሉ እየተደረገ መሆኑንም የገለፀው መግለጫው፥ ጉዳያቸውም ተገቢውን ሂደት ጠብቆ እየተጣራ ለፍርድ እንዲቀርቡ እየተደረገ ይገኛል ብሏል።
መንግስት በሆደ ሰፊነት በተደጋጋሚ ጊዜ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ከቁብ ያልቆጠሩ ኃይሎችን መግታት የሚቻለው የህግ የበላይትን በማስከበር ብቻ ነው ያለው መግለጫው፥ ሁሉም ዜጋና የተለየ አመለካከት ያላቸው ወገኖችም መብትና ጥቅሞቻቸውን ማስከበር የሚችሉት የህግ የበላይነት ሲረጋገጥና ሰላም ሲሰፍን ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የዜጎች ሰላም፣ ደህንነትና የሀገር ቀጣይነት የሚረጋገጠው የህግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው፡፡ በመላ ኢትዮጰያ የሚገኘው ዜጋ በሰላም ወጥቶ የመግባት መብቱ እንዲከበርና ደህንነቱ እንዲጠበቅ የህግ የበላይነትን ማስፈን ደግሞ ህዝብ ለመንግስት የሰጠው ሃላፊነት ነው። የዜጎች ነፃነትና ዲሞክራሲም መስፈን የሚችለዉ የትኛውም ጉልበት አለኝ የሚል አካል ከህግ በታች መሆኑ እስከተረጋገጠ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ነፃነትንና መብትን ከለላ በማድረግ የሚፈፀም የትኛውም አይነት እኩይ ተግባርን መንግስት አይታገስም፡፡ መንግስት በሆደ ሰፊነት በተደጋጋሚ ጊዜ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ከቁብ ያልቆጠሩ ኃይሎችን መግታት የሚቻለው የህግ የበላይትን በማስከበር ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ዜጋና የተለየ አመለካከት ያላቸው ወገኖችም መብትና ጥቅሞቻቸዉን ማስከበር የሚችሉት የህግ የበላይነት ሲረጋገጥና ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነው፡፡