ዴንማርክ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ አጋሯ እንደመሆኗ የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለፀች
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የዴንማርክን የልማት ትብብር ሚኒስትር ፍሌሚንግ ሞለር ሞርቴንሰንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግርዋል።
በዚህ ወቅት አቶ ደመቀ ዴንማርክ ለኢትዮጵያ እያደረገችው ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
በቀጣይም ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል የጠየቁ ሲሆን፥ በመንግሥት በኩል ለተፈጠሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየተወሰዱ ስላሉ እርምጃዎች ገለፃ አድርገዋል።
መንግሥት ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ተግባራዊ የተደረገው የተኩስ አቁም ውሳኔ እና ከአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የተጀመሩ ጥረቶች ከጫፍ እንዲደርሱ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠውላቸዋል።
አክለውም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ስለመሆኑ፣ ከፍተኛ ፖለቲከኛ እስረኞች መፈታታቸው፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትን በተመለከተም የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁም የምርመራ እና የማጣራት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ነው የገለፁት።
በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተፈጠረው ግጭት እና በድርቅ ምክንያት አሁን ላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰብአዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች እንዳሉ በማንሳትም ዓለም አቀፉ ለጋሽ ማህበረሰብ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ድጋፉን እንዲያስፋፉ ነው የጠየቁት።
የዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትሩ ፍሌሚንግ ሞለር ሞርቴንሰንን በበኩላቸው፥ አሁን ላይ ለችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሔ ለመስጠት መንግስት የጀመራቸው ጥረቶች አበረታች ናቸው ብለዋል።
ሀገራቸውም ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ አጋሯ እንደመሆኗ የምትሰጠውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
የታዳሽ ኃይል እና ድርቅን መከላከልን ጨምሮ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ መርሐ-ግብሮች እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚሰሩ ሥራዎች ላይ የሚኖረን ትብብር ይጠናከራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ላጋጠማት ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በመንግሥት በኩል የተጀመሩ ሥራዎችን እንደግፋለን ሲሉም ቃል ገብተዋል።
አቶ ደመቀ በመጨረሻም መንግሥት ለሰላም በቁርጠኝነት እየሰራ ቢሆንም፥ የህወሓት ቡድን ግን አሁንም ህጻናት እና እድሚያቸው የገፉ ሰዎችን ሳይቀር እየመለመለ ነው ብለዋል።
ቡድኑ አሁንም ድጋሚ ለሌላ ጥፋት እየተዘጋጀ በመሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና ሊፈጥርበት ይገባል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።