ኢትዮጵያ ለመረጋጋቷ እየወሰደች ያለችውን እርምጃዎች እንደምታበረታታ ዴንማርክ አስታወቀች
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ የአህመድ ሽዴ ከዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትር ፍሊሚንግ ሞለር ሞርቴንሰን ጋር ተወያዩ።
በገንዘብ ሚኒስቴር በተካሄደው ውይይት ላይ የዴንማርክን የቆየ የኢትዮጵያ የልማት አጋርነት ያነሱት አቶ አህመድ፥ በግጭት ወቅትም ሀገሪቱ ይህንን የልማት ድጋፏን በመቀጠሏ አመስግነዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ ሀገሪቱ ወደ ሰላም እያደረገች ያለችውን ጉዞ፣ ህዝብ ማእከል ባደረገ መልኩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መስራተ ወሳኝነት ላይ መክረዋል።
በተጨማሪም ከዓየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ የታዳሽ ሀይል ልማት፣ ድርቅ መከላከልን እና በዓየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ የሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን መድረስ በሚቻልልበት ሁኔታ ላይ እንዲሁ ተወያይተዋል።
የተከሰተው ግጭት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና መሠረተ ልማት ላይ እንዲሁም በህዝቡ የኑሮ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ያስረዱት ሚኒስትሩ፥ በግጭት የተጎዱ አከባቢዎች እንዲያገግሙ በመንግስት እየተከናወነ ስላለው ስራ አብራርተዋል።
እነዚህ በግጭት የተጎዱ አካባቢዎች በአግባቡ ያገግሙ ዘንድ ግን የለጋሽ ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት።
የዴንማርክ የልማት ትብብር ሚኒስትር ፍሊሚንግ ሞለር ሞርቴንሰን በበኩላቸው፥ የሀገራቸው ፍላጎት ኢትዮጵያ ወደ መረጋጋት እንትመጣ መሆኑን አንስተው፥ ይህ እንዲሆን ለማስቻል የተወሰዱ እርምጃዎችንም እንደምታበረታታ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የሰብዓዊ እርዳታው አቅርቦቱ ዘላቂ እንዲሆንም እንዲሁም ዴንማርክ ድጋፏን ትቀጥላለች ነው ያሉት።
ሚኒስትሮቹ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር አጠናክሮ ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡